በአሽከርካሪነት ሙያ ተቀጥሮ ከሚሰራበት ድርጅት የተሰጠውን ተሽከርካሪ በመሰወር 10 ጎማዎቹን ሸጦ የተሰወረን ግለሠብ ከእነ ግብረ አበሩ በቁጥጥር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን የቂርቆስ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።
ተከሳሽ ቢያብል ታረቀኝ፤ ሠለሞን በየነ ከተባለ ግብረ አበሩ ጋር በመሆን የወንጀል ድርጊቱን የፈጸመው ሐምሌ 21 ቀን 2017 ዓ/ም በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 መስቀል ፍላወር አካባቢ ከሚገኝ የግንባታ ድርጅት ግቢ ውስጥ መሆኑን ፖሊስ አስታዉቋል።
ተጠርጣሪው በድርጅቱ ውስጥ በአሽከርካሪነት ሙያ ተቀጥሮ እየሰራ ሳለ ለስራ የተሰጠውን ኮድ 3 – 32 9 19 ኢት የሆነ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪ ወደ አስኮ አካባቢ በመውሰድ ግምቱ ከ800 ሺህ ብር በላይ የሚያወጣ 10 የተሽከርካሪውን ጎማዎች እና 2 ባትሪዎችን በመፍታት ከሸጠ በኋላ ወደ አማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምስራቅ ጎጃም ዞን ቢቸና ከተማ በመሄድ መሰወሩ ተገልጿል።

ፖሊስ ከግል ተበዳይ መረጃ በመነሳት ባደረገው ብርቱ ክትትል እና ከቢቸና ከተማ ፖሊስ ጋር በመተባበር ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር ማዋልም ተችሏል።
አሽከርካሪው በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላም በተከናወነው ምርመራ የማስፋት ስራ አንድ ግብረ አበሩን እና አስሩን ጎማዎች ገዝቷል የተባለን ላመስግን ቀሬን በቁጥጥር ስር በማዋል ተሽከርካሪውን እና የተሸጡ ጎማዎችንም ማስመለስ መቻሉን ፖሊስ ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በላከዉ መረጃ አስታዉቋል።
ሦስቱም ተጠርጣሪዎች ላይ የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን በማሰባሰብና የምርመራ መዝገቡንም በማደራጀት በዐ/ህግ በኩል ክስ እንደሚመሠረትም በመረጃዉ ተጠቅሷል።