ጋሜና ሹሩባ ተሰርተው፣ አልቦና አምባር በእጃቸው አጊጠው፣ ክታብ እና ድሪ በአንገታቸው አጥልቀው፣ በባህላዊ ጥልፍ ቀሚስ ላይ ቄጤማ በወገባቸው እስረው፣ በሽብሻቦ እና በከበሮ እየደለቁ በሚያምር ዜማቸው ነጻነታቸውን ፍቅራቸውን ይገልጹበታል በሻደይ፡፡
በሻደይ ሰሞን የዋግ ቆነጃጅት በዜማቸው ሙያ መቻላቸውን እና ውበታቸውን እንዲህ ያዜማሉ፡-
ወፌላላ ወፌ ላላዬ (2)
የኛማ ወይዘሮ የሰራችው ዶሮ
ብት ብሎ ሄደ መግላሊቱን ሰብሮ…
እነዚህ ስንኞች በአማራ ክልል በዋግኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን የሚኖሩ ልጃገረዶች በአመት አንድ ጊዜ ሻደይን የሚያደምቁበት ውብ ስነቃላዊ የህዝብ ዜማዎች ናቸው፡፡
በዋግኽምራ እና በአከባቢው የሚኖሩ ልጃገረዶች ከነሀሴ አጋማሽ ጀምሮ በባህላዊ አልባሳት፣ በጌጣጌጥ፣ በሹሩባ፣ እጅ እግራቸውን በእንሶስላ አሙቀው፣ ደምቀውና ተውበው፣ ከሚታዩባቸው ባህላዊ እና ትውፊታዊ በዓላት መካከል የሻደይ በዓል ዋነኛው ነው።
በዋግኸምራ ልጃገረዶች ዘንድ የነሀሴ ወር በጉጉት የሚጠበቅና የነፃነት ወር ሆኖ ነው የሚያልፈው፡፡ በዚህ የልጃገረዶች በዓል የተጣሉት ታርቀው በአንድነት፣ በአብሮነት እና በይቅርታ በጋራ ለሳምንታት እያዜሙና መልካም ምኞትን እየተመኙ የሚያሳልፉበት ጊዜ ነው፡፡
ይህ በዓል ከትውልድ ትውልድ እየተሻገረ የመጣ የልጃገረዶች የነፃነት ባህልና ወግ እሴት ሲሆን፣ ከዋግኽምራ በተጨማሪ በላሊበላ አሸንድዬ፣ በራያቆቦ ደግሞ ሶለል በሚል የተለያ መጠሪያ በድምቀት እየተከበረ ይገኛል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የሻደይ በዓል ከላይ ከተጠቀሱት አካባቢዎች በተጨማሪ በባህር ዳር እና በአዲስ አበባ ከተማ ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች በድምቀት መክበር ጀምሯል።
እንደነዚህ አይነት በዓላት የአካባቢን ትውፊቶች፣ የአገርን ባህል እና ገፅታ ከመገንባት በተጨማሪ ለቱሪዝም መስህብ ከፍተኛ ሚና እንደሚያበረክቱ ይታመናል።
ዘንድሮ ይህን በታሪካዊ እና በባህላዊ ድምቀቱ የሚታወቀውን የሻደይ የልጃገረዶች አመታዊ በዓል አከባበርን በተመለከተም የዋግኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን የኮሚንኬሽን መምሪያ ሀላፊ አቶ ከፍያለው ደባሽ ሃሳባቸውን ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል ሚዲያ አጋርተውናል፡፡
ሻደይ ልጃገረዶች የሚከውኑት አመታዊ ክዋኔ መሆኑን ገልፀው፣ ዘንድሮም ከነሃሴ 16 እስከ 21 /2017 ዓ.ም ድረስ ባሉት ተከታታይ ቀናት በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል ብለዋል።
“ሻደይ” የሚባለው ልጃገረዶች በወገባቸው ላይ የሚያስሩት ቅጠል ወይም ቄጤማ መሆኑን የገለጹት ሀላፊው፣ ልጃገረዶች በዓሉን ሲያከብሩ በመጀመሪያ ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ ፀሎት ከአደረጉ በኋላ በሚያምር ዜማና ጭፈራ እያዜሙ ወደ መጫዎቻ ቦታቸው ይመለሳሉ ብለዋል፡፡
የሻደይ በዓል የአብሮነት፣ የአንድነት እና የመተባበር እሴት መገለጫ መሆኑን የገለጹት ሀላፊው፣ የዘንድሮውን የሻደይ በዓልን ለማክበርም ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሻደይ በዓል ትውፊቱን ጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ እና በዩኔስኮ እንዲመዘገብ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም የኮሙኒኬሽን መምሪያ ኃላፊው ጠቁመዋል።
በሰቆጣ ከተማ በዓሉን ለማክበር የሚመጡ እንግዶችንም በዋግ ባሕል እና ወግ መሰረት ለመቀበል ሰፊ ዝግጅት መደረጉንም አቶ ከፍያለው ተናግረዋል፡፡
በአለኸኝ አዘነ