የኢትዮጵያ ሐኪሞች ማህበር ከኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ጋር በመተባበር በበጎ ፈቃድ የነፃ ህክምና አገልግሎት እየሰጠ ነው፡፡
የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ኒዕመተላህ ከበደ በክፍለ ከተማው የአቅመ ደካማ ቤቶችን ማደስን ጨምሮ የተለያዩ የበጎ ፈቃድ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ በመርሀግብሩ ላይ ገልፀዋል፡፡
በክፍለ ከተማው እየተሰጠ ያለው የነፃ ህክምና መርሐ ግብር የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት አካል ሲሆን፣ 1 ሺህ 500 ዜጎችን ተደራሽ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኅብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ይመር ከበደ፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ያለምንም ልዩነት ሀሳብን ከመስጠት ጀምሮ የሚለገስ ነፃ አገልግሎት ነው ብለዋል።
በአገልግሎቱ ለተሳተፉ የጤና ባለሙያዎች እና ተቋማትም ምስጋና አቅርበዋል።
የጤና ሥራ የአንድ ወቅት ብቻ አለመሆኑን የገለፁት የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ አማካሪ ወ/ሮ ብርቱካን መሀመድ፣ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በጤናው ዘርፍ በስፋት እንደሚሰራበት አስገንዝበዋል፡፡
በፅዮን ማሞ