በቅርቡ የተመረቀው የአራት ኪሎ- እንጦጦ ኮሪደር ልማት የሽሮ ሜዳ አካባቢ የሚታወቅበትን የጥበብ ሥራ እና ሀገራዊ ባህልን ባማረ መልኩ በአደባባይ የገለጠ ነው ሲሉ ነዋሪዎች ለኤ ኤም ኤን ተናገረዋል፡፡
በርካቶች የሽመና ውጤቶችን ሲፈልጉ ወደ ሽሮ ሜዳ መምጣት የተለመደ ነው ያሉት የአካባቢው ነዋሪ ወ/ሮ አስካለ ገብሬ፣ ቀደም ሲል የነበረው የአካባቢው ገፅታ ያልተስተካከለ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡
አሁን ላይ አካበቢውን እና በአካባው ያለውን ጥበብ የገለጠ ልማት በመሠራቱ ቀደም ሲል ከሚያውቁት እንደተለየባቸው ነው የተናገሩት፡፡
ሌላኛው የአዲስ አበባ ነዋሪ አቶ አለማየሁ ታደሰ፣ የሽሮ ሜዳ ድንቅ ሙያዋና ጥበቧ በተጎሳቆለ ሁኔታ ውስጥ የቆዩ በመሆናቸው ተሸፍነው መክረማቸውን በማንሳት፣ ቀጣዩ ትውልድ እና ዓለም እንዲያውቃት የሚያስችል ሥራ በመሠራቱ ውበቷ በግልጥ እየታየ ነው ብለዋል፡፡
የመዝናኛ ሥፍራዎች፣ የአካባቢውን የጥበብ እጆቸ ሙያ የሚየሳዩ ናሙናዎች በጥሩ ዲዛይን በአደባባይ መቀመጣቸው እና የመስታወት ሱቆች መሰራታቸው ይበልጥ እንድንታወቅ አድርጎናል ያሉት ሌላኛዋ ነዋሪ ወ/ሮ ወይንሸት ማሳ፣ በዚህም ደስተኞች ነን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የሽሮ ሜዳን እደ ጥበብ የሚያሳዩ ናሙናዎቸ የኮሪደር ልማቱ አካል ተደርገው መሠራታቸው የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ጎብኚዎች ወደ አካባቢው ሲመጡ ያለማንም ማብራሪያ ሥፍራውን እንዲረዱት የሚያስችል መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡

ውብ የሀገር ባህል ልብሶች የሚመረቱበት አካባቢው፣ አልባሳቱ በማይታዩ፣ በተከለሉ እና ለዓይን በማይማርኩ የንግድ ማዕከላት ውስጥ እንደነበሩ የሚያስታውሱት ነዋሪዎቹ ኮሪደር ልማቱ ለነዚህ የጥበብ ውጤቶች መልካም እድል ይዞላቸው እንደመጣም ይናገራሉ፡፡
አዲስ አበባን እየቀየራት ያለው የኮሪደር ልማት በብዙ መልኩ ሊገለጽ የሚችል ለውጥ ማምጣቱንም አንስተዋል፡፡
በተለይም ኢትዮጵያዊ ባህሎች፣ እሴቶች እና ቅርሶችን ይበልጥ አስውቦ ለትውልድ ከማስተላለፍ አንፃር እየተወጣ ያለው ሚና በእጅጉ ከፍተኛ እንደሆነም ነዋሪዎቹ ይስማሙበታል፡፡
በማሬ ቃጦ