በጎርፍ የፈረሰውን የጌደብ ወንዝ ድልድይ በተገጣጣሚ ብረት አገልግሎት ለማስጀመር እየተሰራ መሆኑን የምስራቅ ጎጃም ዞን መንገድና ትራንስፖርት መምሪያ ገለጸ።
ከኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የደብረ ማርቆስ መንገድ ጥገና ዲስትሪክት ጋር በመነጋገር ተገጣጣሚ ድልድይ ለመስራት ጥረት እየተደረገ ነው ተብሏል።
የመምሪያው ኃላፊ አቶ ማናየ አዳነ፣ ትናንት ማታ ጮቄ የተባለው ከፍተኛ ተራራ አካባቢ የጣለው ከባድ ዝናብ ያስከተለው ከፍተኛ ጎርፍ ድልድዩን በመስበር ያፈረሰው መሆኑን አረጋግጠዋል።
በመሆኑም ከኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የደብረ ማርቆስ መንገድ ጥገና ዲስትሪክት ጋር በመነጋገር፣ በአፋጣኝ ተገጣጣሚ ድልድይ በመስራት ስራ ለማስጀመር ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል።
ድልድዩ ተሰርቶ አገልግሎት እስኪጀምር ተጓዦች አማራጮችን እንዲጠቀሙ ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።