የእስራኤል ዕቅድ ጋዛን ነፃ ለማውጣት እንጂ ለመውረር አይደለም- ቤኒያሚን ኔታኒያሁ

You are currently viewing የእስራኤል ዕቅድ ጋዛን ነፃ ለማውጣት እንጂ ለመውረር አይደለም- ቤኒያሚን ኔታኒያሁ

AMN- ነሐሴ 4/2017 ዓ.ም

በእስራኤል የጸጥታ ካቢኔ የጸደቀው ወታደራዊ ዕቅድ ጋዛን ነፃ ለማውጣት እንጂ ለመውረር አይደለም ሲሉ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ገለጹ፡፡

እስራኤል ጋዛን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር ከያዘችው ዕቅድ በተገናኘ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የጸጥታው ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ መጥራቱን ተከትሎ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸውም፣ ዕቅዱ ጋዛን ለመውረር ሳይሆን ነፃ ለማውጣት ነው ያሉ ሲሆን፣ ዕቅዱንም ጦርነቱን ለማስቆም ምርጡ መንገድ ሲሉ ገልጸውታል፡፡

ኔታኒያሁ አያይዘውም፣ በአካባቢው የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እና ስርጭት ከፍ እንዲል የሚያስችል ሦስት ደረጃ ያለው ዕቅድም አቅርበዋል፡፡

በጋዛ የያዙትን ዕቅድ ፍትሃዊ እና ፈጣን በሆነ መንገድ እንደሚያከናውኑ እና በቀዳሚነትም ደህንነቱ የተጠበቀ ከባቢ እንደሚመሰርቱ ገልጸዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ትራምፕ በጋዛ ስላለው ረሀብ የሰጡትን አስተያየት በተመለከተ የተጠየቁት ኔታኒያሁ፣ የፕሬዚዳንቱን ድጋፍ እንደሚያደንቁ በመግለጽ፣ ትራምፕ ታጋቾች እንዲለቀቁ እና ሃማስ በጋዛ መኖር የለበትም ብለዋል ሲሉ አክለዋል፡፡

አያይዘውም በጋዛ ለተከሰተው ረሃብ እና ሞት ሃማስን ተጠያቂ ማድረጋቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

በተያያዘም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የጸጥታው ምክር ቤት እስራኤል በመካከለኛው ምስራቅ የያዘችውን ዕቅድ አስመልክቶ አስቸኳይ ስብሰባውን በኒውዮርክ እያካሄደ ነው፡፡

በስብሰባውም በተመድ የአውሮፓ፣ የመካከለኛው እስያና የአሜሪካ ረዳት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ሚሮስላቭ ጄንቺ፣ በፍልስጤም ግዛት የሚገኙ ሰዎች የከፋ አደጋ እንደሚደርስባቸው ገልጸዋል።

ሐሙስ የጸደቀው የእስራኤል አዲስ ባለ አምስት ነጥብ ዕቅድ ‘ሌላ አደገኛ የግጭት መባባስ’ እንደሚያስከትልም አስገንዝበዋል።

እስራኤል በጋዛ የያዘችው ዕቅድ አምስት ዓላማዎች፤ ሃማስን ትጥቅ ማስፈታት፣ ታጋቾችን ማስለቀቅ፣ አካባቢውን ከወታደራዊ ኃይል ነፃ ማድረግ፣ ጸጥታውን መቆጣጠር እና የሲቪል አስተዳደር መመስረት መሆኑን የኔታኒያሁ ጽሕፈት ቤት ከትናንት በስቲያ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review