ስላሳለፉት መከራ እና ውጣውረድ እንባ በተሞላ ድምፃቸው ይናገራሉ ወ/ሮ ሃረጓ ተክለወልድ።
በእድሜ ብቻ እዳላረጁ ገፅታቸው ያሳብቃል። ከብርድ እና ቁር በማያስጠልል ባዘመመች ጎጆ ውስጥ ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ኑሮ እስክ 11 የቤተሰብ አባላትን ይዘዉ ለበርካታ አመታት ህይወታቸውን ገፍተዋል።
ወይዘሮዋ ሃረጓ ባለቤታቸው ከሞት ከተለዩዋቸው በኃላ ጥሩ ኑሮ እንደሌላቸው ይገልጻሉ። ዝናብ እና ውርጭ በሚያስገባው ደሳሳ እና በዘመመ ጎጃቸው ማሳለፋቸውን ይገልጻሉ።
የጎጃቸው ጣሪያው ዝናብ ያስገባል። ይህንን ለመከላከል በየቦታው መዘፍዘፊያ እየደቀኑ ዘመናትን ገፍተዋል። በተለይ በክረምት ወቅት ከላይ ውሃው ከስር የመፀዳጃ ቤት ፍሳሽ እየጠረጉ ቀንና ሌታቸውን እንደሚገፉ ኑሮ እና ችግር በስረጃቸው አሳዛኝ ድምጻቸው ተናግረዋል።
በወይዘሮ ሐረጓ ላይ ያረፈው የችግር አለንጋ ለጎረቤታቸውም አላንቀላፋም። ሰባት ቤተሰብ ያላቸውም ወ/ሮ አያህሉሽም ደገፋ የችግሩ ሰለባ ናቸው።
በጋም አልፎ ክረምት ሲገባ የእድሜ እኩሌታቸውን የሰቀቀን ህይወትን አሳልፈዋል። ወይዘሮዋ እንደሚናገሩት ፣እሳቸው ቤት ሳይኖሩ ዝናብ ከጣለ ሰቀቀን እንደሚይዛቸው ፣ ለዓመታት ተራራን የመግፋት ያህል ከብዷቸው መዝለቃቸውን ተናግረዋል።
ወ/ሮ ሐረጓን ጨምሮ 12 አባወራዎችን የሚኖርበት በአማካይ ከአምስት እስከ አስረአንድ የቤተሰብ አባላትን የያዘ መንደር በችግር ውስጥ አሳልፈዋል።
እነዚህ ነዋሪዎች በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 በተለምዶ ቄራ መስኪድ ተብሎ የሚጠራበት አከባቢ ለዘመናት በማይመች ሁኔታ ኖረዋል።
እነዚህ እናቶች በበጎ ፍቃደኞችን አማካኝነት ከነበሩበት ህይወት እንዲወጡ ህንፃ ተገንብቶ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል።
የፈጣሪ ፍቃድ ሆኖ በአዲሱ ቤታቸው ገብተው የበጎፍቃደኞችን ለመመረቅ መጓጓታቸውን እነዚህ እናቶች ጉጉታቸውን ተናግረዋል።
ችግሩን የተረዱት የአከባቢው ነዋሪዎች እና ከሚመለከታው የመንግስት አካላት ጋር በመሆን ጨለማ ባጠላባቸው ቤቶች ላይ ዳግም ብርሀንን ፈንጥቀዋል።
የበጎ ፍቃድ አስተባባሪዋ ወ/ሮ እመቤት ሀይሉ እንደሚናገሩት፣ በበጎ ፍቃደኞች የዜጎች ህይወት ተቀይሮ ማየት ያስደስታል ብለዋል።
የሚኖሩበት ሲታይ በቶሎ ግንባታው አልቆ በቶሎ ወደቤታቸው እንዲገቡ ክትትል እንደሚያደርጉ ያስረዱት ሌላኛው የበጎ ፍቃድ አስተባባራ አቶ አብነት ተስፋዬ ናቸው።
በሔለን ተስፋዬ