በ2017 በጀት ዓመት ከ308 ቢሊየን ብር በላይ ግዥ በኤሌክትሮኒክ የግዥ ስርዓት መፈፀሙን የፌዴራል መንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን አስታወቀ።
በ2017 በጀት ዓመት የመንግስት ግዥ ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሮኒክ ስርዓት ማከናወን መቻሉ ተገልጿል።
የፌዴራል መንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መሰረት መስቀሌ እንዳሉት፤ በበጀት ዓመቱ የመንግሥት ግዥና አስተዳደር ሥርዓትን ዘመናዊ ከማድረግ አንፃር አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል።
በተጠናቀቀው በጀት አመት በ169 የፌዴራል ባለበጀት ተቋማትና 93 ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች የኤሌክትሮኒክ ግዥ ስርዓት ተግባራዊ መደረጉን ማስታወቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በዚህም በ2017 በጀት ዓመት 308 ነጥብ 75 ቢሊየን ብር በኤሌክትሮኒክ የግዥ ስርዓት የተፈፀመ ሲሆን 300 ቢሊየን ብር በጨረታ 8 ነጥብ 75 ቢሊየን ብሩ ደግሞ ዋጋ በማቅረብ የግዥ ሂደት መከናወኑን አብራርተዋል።
በ2016 በጀት ዓመት በኤሌክትሮኒክ ስርዓት የተከናወነው የመንግስት ግዥ 65 በመቶ ሲሆን በ2017 በጀት አመት ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሮኒክ የግዥ ስርዓት መፈጸሙን ተናግረዋል።
የኤሌክትርኒክ የግዥ ስርዓት አገልግሎትን በማቀላጠፍ፣ እንግልትን በመቀነስና አሰራርን በቴክኖሎጂ በመደገፍ ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ መሳካት ማሳያ ከሚሆኑ አገራዊ የዲጂታል አሰራሮች አንዱ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
በ2017 በጀት አመት የግዥ ስርዓታቸው ሙሉ ለሙሉ በኤሌክትሮኒክ ካከናወኑ ተቋማት መካከል የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ እና የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ይገኙበታል።
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ባለስልጣኑ ከ2015 ጀምሮ የኤሌክትሮኒክ ግዥ ስርዓትን ተግባራዊ ማድረጉን አስታውሰዋል።

ተቋሙ በ2017 በጀት ዓመት ከ960 ሚሊየን ብር በላይ ግዥ በኤሌክትሮኒክ ግዥ ስርዓት የፈጸመ ሲሆን አሰራሩ ግልፅ፣ የማያሻማ፣ ብልሹ አሰራርን ያስቀረ፣ ቀልጣፋ እና ወጪን በማዳን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ማስገኘቱን ነው ያስረዱት።
የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ደረጄ እንግዳ (ዶር) እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከጥቃቅን ግዥዎች በስተቀር ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሮኒክ የግዥ ስርዓት አከናውኗል።
ዩኒቨርሲቲው ከፈጸመው የ357 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ግዥ 269 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የሚሆነውን በኤሌክትሮኒክ የግዥ ስርዓት መፈጸሙን አስረድተዋል፡፡
አሰራሩ አገልግሎቱን ቀልጣፋ፣ ፍትሃዊና ወጪ ቆጣቢ በማድረግ ትልቅ ሚና መጫወቱንም ጠቁመዋል።