የሕዳሴ ግድብ የበርካታ ዜጎችን የኤሌክትሪክ ፍላጎት የሚያረጋግጥ የአፍሪካ የማንሰራራት ዘመን ምልክት ነው

You are currently viewing የሕዳሴ ግድብ የበርካታ ዜጎችን የኤሌክትሪክ ፍላጎት የሚያረጋግጥ የአፍሪካ የማንሰራራት ዘመን ምልክት ነው

AMN ነሐሴ 5/2017

የኢትዮጵያ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ የበርካታ ዜጎችን የኤሌክትሪክ ፍላጎት የሚያረጋግጥ የአፍሪካ የማንሰራራት ዘመን ትልቅ ምልክት መሆኑን የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዝዳንት አቶ ዛዲግ አብርሃ ገለጹ።

የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አመራር አባላት ለሦስት ቀናት የሚቆይ ስልጠና መሰጠት ጀምሯል።

የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዝዳንት አቶ ዛዲግ አብርሃ፥ በሀገራዊ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ የኤሌክትሪክ አቅርቦትና ማመንጨት፣ በመሪነት ሚና፣ ሀገር ፍቅርንና አገልጋይነትን በሚዳስሱ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ስልጠና እየሰጡ ይገኛል።

በስልጠና የመነሻ ጽሁፋቸው፥ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨትና የማከፋፈል ተግባር የአንድ ሀገር ሁለንተናዊ የልማት ማሸጋገሪያ ሞተር ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የምስራቅ አፍሪካ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት አቅም መሆን እንደቻለችም ገልጸዋል።

የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጩና የሚያከፋፍሉ ተቋማት የሀገርን ሁለንተናዊ የልማት እጣ ፋንታ የሚወስኑ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የኤሌክትሪክ ኃይል አመንጪና አከፋፋይ ተቋማት የዘመናዊ መንግስት የመኖር መገለጫ ናቸው ሲሉ አስረድተዋል።

የተቋማቱ ስኬታማ አገልግሎትም የኢኮኖሚ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፖለቲካ፣ ጂኦግራፊና የዲፕሎማሲ ፋይዳ እንዳላቸው አንስተዋል።

የኤሌክትሪክ ኃይል አመንጪ ግድቦችና ባለስልጣን መስሪያ ቤቶች ለሁለንተናዊ የሀገር ልማትና ብልጽግና ሁነኛ መሳሪያ እንደሆኑም አብራርተዋል።

የኤሌክትሪክ ኃይል አቅም በድህነትና ብልጽግና መካከል ያለ ድልድይ ነው ያሉት አቶ ዛዲግ፥ በዚህም የኤሌክትሪክ ኃይል ብልጽግና የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ያጸናል ብለዋል።

ታላቁ የሕዳሴ ግድብም በርካታ ዜጎችን ከኤሌክትሪክ ድህነት ወደ ኤሌክትሪክ ብልጽግና የሚያሸጋግር ብሔራዊ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል።

የኤሌክትሪክ ኃይል ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ የቀጣናውን ሀገራት የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትና የልማት ትስስር እውን ማድረግ የኢትዮጵያ አብሮ የማደግ የውጭ ጉዳይ ፖሊስ ማጠንጠኛ መሆኑንም አንስተዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ማመንጫም ብሔራዊ ኩራትና የአፍሪካ የማንሰራራት ዘመን ትልቅ ምልክት መሆኑን አስገንዝበዋል።

የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨትና የማከፋፈል አቅምን ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ የኤሌክትሪክ ሀይል ልማትና ፉክክርን ታሳቢ በማድረግ ተሻጋሪ ርዕይ ቀርፆ መስራትና መምራት እንደሚያስፈልግ መናገራቸዉን ኢዜአ ዘግቧል።

በስልጠናው ላይ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ጌቱ ገረመውን ጨምሮ የአገልግሎቱ የማዕከልና የሪጅን ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review