የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዋሺንግተን ዲሲ የሚታዩ ወንጀሎችን ለመከላከል በሚል በከተማዋ የሚገኙ ቤት አልባ ሰዎች በፍጥነት ከተማዋን ለቀው እንዲወጡ ጠይቀዋል።
የከተማዋ ከንቲባ ሙሬል ቦውሰር ግን በከተማዋ ያለው ወንጀል እየቀነሰ መምጣቱን በማስተባበል፤ ትራምፕ ከተማዋን ከባግዳድ ጋር ማነፃፀራቸውን “የተጋነነ” በማለት ተችተዋል።
ፕሬዝዳንቱ በትሩዝ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልእክት ከተማዋን ለቀው ለሚወጡት ቤት አልባ ሰዎች ከከተማዋ የራቀ መቆያ ቦታ እንደሚሰጡ፤ ወንጀለኞችን ደግሞ ወደ ማረሚያ ቤቶች እንደሚወስዱ አስታውቀዋል።
ትራምፕ ባለፈው ወር ቤት የሌላቸውን ሰዎች በቀላሉ በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚያስችል ትዕዛዝ የፈረሙ ሲሆን፤ ባለፈው ሳምንት የፌዴራል ፀጥታ አካላት በዋሽንግተን ዲሲ ጎዳናዎች እንዲሰማሩ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።
የፌደራል የፀጥታ አካላቱ ከዩኤስ ፓርክ ፖሊስ፣ ከመድሃኒት ቁጥጥር አስተዳደር፣ ከኤፍቢአይ እና ከዩኤስ ማርሻል የተውጣጡ እንደሚሆኑ ቢቢሲ ዘግቧል።
በዋሺንግተን ዲሲ የመኖሪያ ቤት እጦትን ለመቀነስ የሚሰራው ኮሚኒቲ ፓርትነርሺፕ እንደገለፀው፤ በከተማዋ ካሉት 3 ሺህ 782 ቤት አልባ ሰዎች መካከል 800 የሚሆኑት በጎዳና የሚያድሩ እና ቀሪዎቹ በሕዝብ እና ድንገተኛአደጋ መጠለያዎች ያሉ መሆናቸውን ጠቁሟል።
በፈረንጆቹ 2022 ፕሬዝዳንቱ ባደረጉት ንግግር፤ ቤት አልባ ሰዎችን ከከተማዎች ውጪ ወደሚገኙ ደረጃቸውን የጠበቁ መጠለያዎች እንደሚያዛውሩ መግለፃቸውን ዘገባው አስታውሷል።
በወርቅነህ አቢዮ