የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች በሠላም እና ኢኮኖሚ ግንባታ ላይ በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ አቶ አደም ፋራህ ገለፁ

You are currently viewing የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች በሠላም እና ኢኮኖሚ ግንባታ ላይ በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ አቶ አደም ፋራህ ገለፁ

AMN- ነሐሴ 6/2017 ዓ.ም

በአፍሪካ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመካከላቸው ጠንካራ ትብብር በመፍጠር በሠላም እና ኢኮኖሚ ግንባታ ረገድ በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ገልጸዋል፡፡

በጋና አክራ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው 12ኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ ላይ የተገኙት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ በአፍሪካ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሊያተኩሩባቸው ይገባል ያሏቸውን ሶስት ስትራቴጂያዊ ጉዳዮችን አብራርተዋል፡፡

የመጀመሪያው መሪው ፓርቲ እና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ተቀራርበው የሚነጋገሩበት ተቋማዊ አሰራር ተበጅቶ በሠላም፣ ፀጥታ እና ኢኮኖሚ ግንባታ ላይ በጋራ ሊሠሩ ይገባል የሚል ነዉ፡፡

የወጣቶችን እውነተኛ ጉዳይ አሸናፊ ለማድረግ በትምህርት ተሳትፎ ፣ ፈጠራ እና የፖለቲካ ተሳትፎን በማረጋገጥ ፖለቲካው በወጣቶች እንዲቀረፅ ማስቻል ሁለተኛው ስትራቴጂካዊ አካሄድ ሊሆን እንደሚገባም አንስተዋል፡፡

ቴክኖሎጂን፣ ታዳሽ ሀይል እና ፈጠራን በመጠቀም፣ ባህላዊ የዕድገት አካሄዶችን መተው እና አረንጓዴ እና ዲጂታል ሽግግር በመምራት ተወዳዳሪ እና ዘላቂ ኢኮኖሚን መገንባት የሚለው ሶስተኛው ስትራቴጂ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

በአፍሪካ መፃዒ ሁኔታ ትልቅ ተስፋ አለኝ ያሉት አቶ አደም ይህም አዲሱ ትውልድ፣ መሪዎቿ እና ዜጎቿ በቅንጅት፣ በአካታችነት እና በውጤት የሚያምኑ በመሆናቸው ነው ብለዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎችን ራዕይ እና መርህ ባለው አመራርነት በማጠናከር እንዲሁም ለአካታች ልማት ቁርጠኛ በመሆን ተስፋችንን ዕውን ማድረግ እንችላለንም ነው ያሉት ፡፡

በማሬ ቃጦ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review