ፓሪሰን ዠርማ ከ ቶተንሃም የአውሮፓ ሱፐር ካፕን ለማንሳት ዛሬ ይጫወታሉ

You are currently viewing ፓሪሰን ዠርማ ከ ቶተንሃም የአውሮፓ ሱፐር ካፕን ለማንሳት ዛሬ ይጫወታሉ

AMN – ነሃሴ 07/2017 ዓ.ም

በጣልያን ኡዲኔ ከተማ የሚገኘው ስታዲዮ ፍሪኡሊ የአውሮፓ ሱፐር ካፕ ጨዋታን ለማስተናገድ ተዘጋጅቷል ፡፡ የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ አሸናፊው ፓሪሰን ዠርማ እና የዩሮፓ ሊግ አሸናፊው ቶተንሃም ሆትስፐርስ በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ዋንጫውን ለማንሳት ይፋለማሉ ፡፡

ያሳለፍነው ግንቦት ወር ላይ የተጠናቀቀው የ2024/25 የውድድር ዓመት ፓሪሰን ዠርማ መቼም የማይፋቅ ውብ ታሪክ የፃፈበት ሆኖ አልፏል ፡፡ የፈረንሳዩ ክለብ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የቻምፒየንስ ሊግ ያነሳበት የሊግ 1 እና ኩፕደ ፍራንስ ዋንጫዎችን ያሸነፈበትን የውድድር ዓመት አሳልፏል ፡፡

የበርካቶችን ቀልብ የገዛ ውብ እግር ኳስ እየተጫወተ የሦስትዮሽ ድል ያሳካው ፒ ኤስ ጂ ዘንድሮም ይህን ታሪክ ለመድገም ተዘጋጅቷል ፡፡

በባሎን ድ ኦር 30 እጩ ውስጥ ዘጠኙን ያስመረጠው ፓሪሰን ዠርማ ከግብ ጠባቂው ጂያንሉጂ ዶናሩማ በስተቀር ታሪክ የሰራው ስብስቡ አልተጓደለም ፡፡

ዶናሩማን ያልፈለገው ሊውስ ኤነሪኬ የሊሉ ግብጠባቂ ሉካስ ቼቬሌ ፈርሞለታል ፡፡ በዛሬውም ጨዋታ በስብስቡ ያልተካተተው ጣልያናዊ ግብ ጠባቂ ተክቶ ይሰለፋል ተብሎ ይጠበቃል ፡፡

በዓለም የክለቦች ዋንጫ ላይ ተሳትፎ በፍፃሜው በቼልሲ የተሸነፈው ፒ ኤስ ጂ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱ በጣም አጭር ነበር ፡፡ የዛሬውን ጨዋታ የሚያደርገው ምንም ዓይነት የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ሳያከናውን ነው ፡፡

ቶተንሃም የተጠናቀቀውን የውድድር ዓመት ያሳለፈው ሁለት መልክ ይዞ ነው ፡፡ በአንድ በኩል ከ 17 ዓመት በኋላ ዋንጫ ያሸነፉበት በሌላ በኩል በሊጉ 17ኛ ሆነው የጨረሱበት ሆኖ አልፏል ፡፡

የክለቡ ባለስልጣናት ዋንጫውን ሳይሆን የሊግ ደረጃቸውን በማየት አንጅ ፖስቴኮግሉን አሰናብተው የብሬንትፎርዱን አሰልጣኝ ቶማስ ፍራንክን አምጥተዋል ፡፡

የሰሜን ለንደኑ ክለብ ሶን ሁንግ ሚን ወደ ሜጀር ሊግ ሶከር በመላኩ እና ጀምስ ማዲሰን በመጎዳቱ ተተኪዎችን እያሰሰ ይገኛል ፡፡

ቶማስ ፍራንክ ከሊውስ ኤነሪኬ የተሻለ ጊዜ ኖሯቸው ቡድናቸውን ቢያዘጋጁም የፒ ኤስ ጂ ስብስብ የላቀ ደረጃ ላይ የደረሰ በመሆኑ ጨዋታውን የማሸነፍ ግምት የተሰጠው ለፈረንሳዩ ክለብ ነው ፡፡

ሁለቱ ክለቦች የሱፐር ካፕን አሸንፈው አያውቁም ፡፡ ፒ ኤስ ጂ እኤአ 1996 በጁቬንቱስ ተሸንፎ ዋንጫውን አጥቷል ፡፡ ቶተንሃም ግን ለሱፐር ካፕ ዋንጫ ሲፋለም የዛሬው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡

ፓሪሰን ዠርማ እና ቶተንሃም በታሪካቸው አንድ ጊዜ ብቻ ተገናኝተዋል ፡፡ በ2017 የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ላይ ተጫውተው ቶተንሃም 4ለ2 ማሸነፍ ችሏል ፡፡

ዘንድሮ ለ50ኛ ጊዜ የሚደረገው የአውሮፓ ሱፐር ካፕ ጨዋታ ምሽት 4 ሰዓት ላይ ይጀምራል ፡፡ ፖርቹጋላዊው ዋና ዳኛ ጆአኦ ፒንሂሮ ጨዋታውን የሚመሩ ይሆናል ፡፡

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review