በማላዊ በተለያዩ እስርቤቶች ውስጥ የነበሩ 210 ኢትዮጵያውያን ከኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ከዓለም አቀፍ ፍልሰተኞች ድርጀት እና ዳር ሳላም ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በመተባበር ከነሐሴ 1- 7 ቀን 2017 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ወደ ሀገር ቤት መመለስ መቻሉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ዜጎቹ ህጋዊ ቪዛ ሳይዙ በህገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ደላሎች በመታለል ከፍተኛ ገንዘብ ጭምር በመክፈል በሞያሌ በኩል ከሀገር በመውጣት የኬንያ እና የታንዛንያ ድንበሮችን በማቋረጥ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመሻገር ጥረት እያደረጉ በሚገኙበት ጊዜ በማላዊ ሀገር የፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር በመዋል ለረዥም ጊዜ እስርቤት ውስጥ የቆዩ ናቸው ተብሏል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የማላዊ መንግስት ጋር በመነጋገር እንደዚሁም የትራንስፖርት ወጪኣቸውን ለመሸፈን ከዓለም አቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅት እና ከኢትየጵያ አየር መንገድ ድጋፍ በማገኘት ዜጎችን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ማድረግ መቻሉን ገልጿል፡፡
መንግሥት ዜጎች በህገወጥ ደላሎች በመታለል ህጋዊ ቪዛ ሳይዙ ወደተለያዩ አገራት በመጓዝ ለተለያዩ ችግሮች እንዳይጋለጡ ራሳቸውን እንዲጠብቁ በዚሁ አጋጣሚ ለማሳሰብ ይወዳል ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።