AMN- ነሐሴ 7/2017 ዓ.ም
ወጣት ዘላለም መላኩ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ነዋሪ ሲሆን፣ ከአሁን ቀደም ከስራ መልስም ሆነ በእረፍት ቀናት አካላዊ እንቅስቃሴዎችን የሚያደርግበትና የሚዝናናበትን ስፍራ በማጣት ሲቸገር እንደነበር ይናገራል፡፡
በአካባቢዉ የሚገኙ ወጣቶችም ሆኑ ነዋሪዎች ከዚሁ ከአካል ብቃት ማዘውተሪያና ከመዝናኛ ስፍራ እጦት የተነሳ የእረፍት ቀናቸውን ቤት ውስጥ ለማሳለፍና ለሱስ ወደሚያጋልጡ ስፍራዎች ጭምር ለመሄድ መገደዳቸውን ይገልጻል፡፡
የአካበቢው ወጣቶች እና ታዳጊዎች እራሳቸውን ለመኪና አደጋ አጋልጠው የዘወትር የስፖርት እንቅስቃሴቸውን ይከውኑ እንደ ነበርም የቅርብ ጊዜ ትውስታው ነው ።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን የኮሪደር ልማቱን ተከትሎ የመዝናኛና የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች በመገንባታቸው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ይገልጻል፡፡
ከሁሉም በላይ በምሽት ከጓደኞቹ ጋር የሚጫወትበትን ዘመናዊ ሜዳ በአቅራቢያው ማግኘቱ እጅግ እንዳስደሰተው ይናገራል፡፡
ከጨርቆስ ሲሳይ ሜዳ አከባቢ እንደመጣ የሚናገረዉ ወጣት አብርሀም አበራ በበኩሉ፣ የአስም ህመምተኛ በመሆኑ እለት እለት ስፖርታዊ እንቅስቃሴ እንዲያደርግ በሀኪም ቢነገረውም ይህን የሚተገብርበት ስፍራ በማጣት ከህመሙ ጋር ለረጅም ጊዜ መቆየቱን ይገልጻል፡፡
በአሁኑ ወቅት ግን በአቅራቢያዉ የተገነባው የመጫወቻ ሜዳ፣ ለጤናው መሻሻል አስተዋፅዖ ከማድረጉም በላይ በቀንም ሆነ በማታ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን እንዲያደርግ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ይገልጻል፡፡
በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 የሚገኘው የመጫወቻ ስፍራ ምሽት 1፡30 አካባቢ በዛ ብለዉ እግር ኳስ ሲጫወቱ የነበሩ ሌሎች ወጣቶችም ቀን ስራ ላይ ውለው ማታ ላይ እግር ኳስ በመጫወት እንደሚዝናኑ ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል ሚዲያ ተናግረዋል፡፡
ሜዳዉ መገንባቱ ከመዝናኛነትና ከአካል ብቃት ባለፈ ከአልባሌ ስፍራዎች እንደታደጋቸው እና ማህበራዊ መስተጋብራቸውንም እንዳጠናከረላቸው ይገልጻሉ፡፡
ቂርቆስ ክፍለ ከተማን ጨምሮ በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ከፍለ ከተሞች ከስራ መልስና በእረፍት ቀናት በየአውራ ጎዳናው ከሚዝናኑ የከተማዋ ነዋሪዎች ባሻገር፣ በምሽት መብራት ደምቀዉ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን የሚያደርጉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችም መመልከት የተለመደ ሆኗል፡፡
በቴሌቭዥን መስኮት ከምናውቃቸው ትላልቅ ሀገራት በስተቀር አዲስ አበባን በመሰሉ ከተሞች በምሽት ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን የሚያደርጉ ነዋሪዎችን እምብዛም መመልከት የተለመደ ባይሆንም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን በኮሪደር ልማቱ በምሽት መብራት ደምቆ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ማደረግ የስልጣኔ መለኪያ እየሆነ መጥቷል፡፡
መዲናዋን እንደ ስሟ አዲስ እና ውብ ከማድረግ በተጨማሪ ከህፃናት እስከ አዛውንቶች ጤናቸው የተጠበቀ ማህበረሰብ ለማፍራት በርካታ የስፖርት ማዘውተሪያዎች ለመገንባት ከተማ አስተዳሩ ተጨባጭ ስራዎችን በዘርፉ መስራት በጀመረ በጥቂት አመታት ውስጥ ከ1ሺህ 530 የሚልቁ ማዘውተሪያዎች ተገንብተዉ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል።
በታምራት ቢሻው