በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ባሳለፍነው ሐምሌ ወር ከ3ሺህ 100 በላይ ታጣቂዎች የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ትጥቃቸውን በመፍታት ወደ ህብረተሰቡ መቀላቀላቸውን የዞኑ ሰላምና ፀጥታ መምሪያ አስታወቀ።
በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በፅንፈኝነት አስተሳሰብና በተሳሳተ መንገድ ለጥፋት ዓላማ የተሰለፉ ሁሉ መንግስት በሆደ ሰፊነት ታግሶ የሰላምን አማራጭ ተቀብለው ወደ መደበኛ ህይወታቸው እንዲመለሱ በተደጋጋሚ ጥሪ አቅርቧል።
በዚህም በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በርካቶች ትጥቃቸውን በማስረከብና ይቅርታ በመጠየቅ የሰላም አምባሳደርና የልማት አርበኛ ለመሆን ቃል እየገቡ የሰላምን መንገድ ተቀብለው ተመልሰዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በክልሉ ሰሜን ሸዋ ዞን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በተመለከተ ኢዜአ ከዞኑ የሰላምና ፀጥታ መምሪያ ሃላፊ ይደሰቱ ክፈተው ጋር ቆይታ አድርጓል።
በዞኑ አንዳንድ አካባቢዎች የጽንፈኛ ቡድኑ እንቅስቃሴ እንደነበር አስታውሰው፤ በተለይም በቅርብ ወራቶች የተሰለፉበት ዓላማ ስህተት መሆኑ እየገባቸው በርካቶች ትጥቃቸውን አስረክበው ወደ መደበኛ ህይወታቸው እየተመለሱ ነው ብለዋል።
በዚህም በሐምሌ ወር 2017 ዓ.ም 3ሺህ 155 በክልሉ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የቀድሞ ታጣቂዎች የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለውና ትጥቃቸውን ፈትተው ሕብረተሰቡን መቀላቀላቸውን ጠቅሰዋል።
የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል በዞኑ ከመርሃ ቤቴ፣ ሚዳ እና ሌሎችም ወረዳዎች በየእለቱ እጃቸውን እየሰጡ ያሉት በርካቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።
በየእለቱ ትጥቃቸውን በመፍታት ሰላምን መርጠው የሚመጡ ታጣቂዎች መኖራቸውን አንስተው፤ ሌሎችም ይህንን መልካም እድል እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል።
የመንግስትና የሕዝብ ተቋማትን በማውደም፣ መንገድ በመዝጋት፣ ህጻናት እንዳይማሩ በማድረግ፣ እናቶች በጤና ተቋም እንዳይወልዱና ሕብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት እንዳያገኝ ለፈጠሩት ችግር በመጸጸት በስራ ለመካስ መዘጋጀታቸውን የቀድሞ ታጣቂዎቹ አረጋግጠዋል ብለዋል።
በሰላማዊ እንቅስቃሴ የመጣው ውጤት እንዳለ ሆኖ በጸጥታ ሃይሉ ጠንካራ የህግ ማስከበር እርምጃ በዘረፋና በጥፋት እንቅስቃሴ ውስጥ የነበረው ፅንፈኛ ቡድን እየተበታተነ መሆኑንም ሃላፊው መናገራቸዉን ኢዜአ ዘግቧል።
የብልፅግና ፓርቲ ምክር ቤት ከሐምሌ 30 እስካ ነሐሴ 2 ቀን 2017 ዓ.ም ያካሄደውን መደበኛ ስብሰባ ተከትሎ ባወጣው መግለጫ፤ ግጭትን ሊያስቀሩ የሚችሉ ሰላማዊ አማራጮችን በሁሉም አቅጣጫ ለመሞከርና በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ለሚወስኑ ታጣቂዎች አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አመላክቷል።
የሰላምን አማራጭ ባለመቀበል በሕዝብና በሀገር ላይ ችግር ለመፍጠር በሚጥሩ አካላት ላይ ጠንካራ የህግ ማስከበር እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን ማረጋገጡም ይታወቃል።