ኢቢሲ አዲስ መተግበሪያ ተጠቅሞ ተደራሽ ለማድረግ የጀመረው ጉዞ ትልቅ ማሳያ መሆኑን ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ተናገሩ

You are currently viewing ኢቢሲ አዲስ መተግበሪያ ተጠቅሞ ተደራሽ ለማድረግ የጀመረው ጉዞ ትልቅ ማሳያ መሆኑን ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ተናገሩ

AMN- ነሐሴ 7/2017 ዓ.ም

ኢቢሲ ከ10 በላይ የይዘት ምንጮችን ከ25 በላይ ዲጂታላይዝድ ሲስተሞችን ተጠቅሞ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተደራሽ ለመሆን የጀመረው ጉዞ ትልቅ ማሳያ ነው ሲሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር እና የኢቢሲ ቦርድ ሰብሳቢ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) በራሱ አቅም ያበለጸገውን የሞባይል መተግበሪያ (አፕ) በዛሬው ዕለት በይፋ አስመርቋል።

በመርሐ-ግብሩ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር እና የኢቢሲ ቦርድ ሰብሳቢ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)፣ የኢቢሲ ዲጂታል አሠራር እና የይዘት ስብጥር የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠብቅ እና ለሌሎችም ሚዲያዎች አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑን ተናግረዋል።

መረጃ የሰዎችን የዕለት ከዕለት ኑሮ በብዙ መልኩ በሚዳስስበት በዚህ ጊዜ፣ ኢቢሲ መረጃን በተለያዩ አማራጮች የሁሉንም መልክ በሚያሳይ መልኩ ተደራሽ ማድረጉ ለኢትዮጵያ ሚዲያ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት መሆኑንም አንሥተዋል።

በማኅበራዊ ሚዲያ መረጃ በሰከንዶች ልዩነት ዓለምን በሚያካልልበት በዚህ ጊዜ፣ የተዛቡ ትርከቶችን የሚያስተላልፉ በርካቶች እንዳሉም ሚኒስትሩ አንሥተዋል።

ይህን መቀልበስ የሚችል፣ የሀገርን መልክ የሚገነባ፣ ዜጎችን የሚያቀራርብ እና ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስከብሩ ይዘቶችን ኢቢሲ በዲጂታሉ ዓለም የሚያደርስ አሠራርን ማጎልበቱ ትልቅ እመርታ ነው ሲሉም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ሚዲያዎች የሐሰት ትርክትን በመመከት፣ የሀገራችንን የዕድገት አውዶች በማሳየት ብሎም ኢትዮጵያዊ ጣዕም ያላቸውን ይዘቶች በማምረት ላይ መሥራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

ለዚህም ኢቢሲ ከ10 በላይ የይዘት ምንጮችን ከ25 በላይ ዲጂታላይዝድ ሲስተሞችን ተጠቅሞ ተደራሽ ለማድረግ የጀመረው ጉዞ ትልቅ ማሳያ እንደሆነም ሚኒስትሩ አንስተዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review