ሀገር አቀፍ የመጅሊስ ምርጫውን ማካሔድ የሚያስችሉ የዝግጅት ስራዎች መጠናቀቃቸውን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የምርጫ አስፈጻሚ ቦርድ አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የምርጫ አስፈጻሚ ቦርድ፣ ዛሬ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጠው መግለጫ፣ ምርጫውን ማካሔድ የሚያስችሉ የዝግጅት ስራዎች መጠናቀቃቸውን አስታውቋል፡፡
ህዝበ ሙስሊሙ ከነሐሴ 9 ጀምሮ በሚካሄደው ሀገር አቀፍ የመጅሊስ ምርጫ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግም የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የምርጫ አስፈጻሚ ቦርድ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የምርጫ አስፈጻሚ ቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ አብዱልዋሲዕ የሱፍ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ የኡለማ፣ የምሁራን፣ የወጣቶች፣ የሴቶች እና የሠራተኛ ማኅበረሰብን የሚወክሉ ተመራጮች ምርጫ ከነሐሴ 9 እስከ11 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ይካሄዳል።
ምርጫውን ግልፅ፣ አሳታፊና አካታች በሆነ መልኩ ለማካሄድ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡
ምርጫው ህዝበ ሙስሊሙን በቅንነትና በታማኝነት የሚያገለግሉ አመራሮች ወደ ኃላፊነት የሚመጡበት ነው ብለዋል፡፡
በመሆኑም ለምርጫ የተመዘገበ ሁሉም ህዝበ ሙስሊም በተጠቀሱት ቀናት በነቂስ ወጥቶ ድምጹን እንዲሰጥ ጥሪ ማቅረባቸውን ተዘግቧል፡፡