የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በ2017 በጀት ዓመት ከ99 ሺህ በላይ አዳዲስ ነጋዴዎች የንግድ ስርዓቱን መቀላቀላቸውን አስታወቋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ንግድ ቢሮ የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ፣ የእውቅና ሽልማት ስነ-ስርአትና የ2018 ዕቅድ ዝግጅት አካሂዷል።
የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ፣ በ2017 በጀት ዓመት የመሠረታዊ ሸቀጦችና ሌሎች አገልግሎቶች ላይ የአቅርቦት ሁኔታ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር ከ30 በመቶ በላይ ጭማሪ አሳይቷል ብለዋል።
የንግድ አሻጥሮችን በመከላከል ረገድም ቢሮው በ39 ሺህ የንግድ አገልግሎት ሰጪዎች ላይ እርምጃ ስለመውሰዱ ተናግረዋል።
ቢሮው በ2017 በጀት ዓመት ከ99 ሺህ በላይ አዳዲስ ነጋዴዎች የንግድ ስርዓቱን መቀላቀላቸውን አስታውቋል።
በአንፃሩ ከንግድ ስርዓቱ የሚወጡ ነጋዴዎች ቁጥር መቀነሱንም አክሏል።
የአዲስ አበባ ከተማ የንግድ ቢሮ በከተማዋ የሚገኙ ከ400 ሺህ በላይ ነጋዴዎች የተሳለጠ አገልግሎትን እንዲያገኙ የዲጂታል አገልግሎት እየሰጠ ስለመሆኑ ነው ኃላፊዋ የገለፁት።
ቢሮው የ2017 በጀት ዓመት እቅዱን 98 በመቶ ማሳካቱም በመድረኩ ተገልጿል።
የንግድ ኢንዱስትሪ እና ቱሪዝም ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጋትዌች ዎር፣ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በ2018 በጀት ዓመት የአቅርቦት ሰንሰለትን ከማሳጠር እና ህገወጥ ንግድን በመከላከል ረገድ ስራውን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በ2017 በጀት ዓመት የላቀ አፈፃፀም ላመጡ ሰራቶኞች ዕውቅናም ሰጥቷል።
በወንድምአገኝ አበበ