ጌትነት እንዳሻው የተባለ ተከሳሽ በየካ ክ/ከተማ ወረዳ 5 ልዩ ቦታው መገናኛ ሠላም ታወር ህንፃ ላይ ቢሮ ተከራይቶ ‹‹ ኤልያና የጉዞና አማካሪ ድርጅት ›› የሚል ህጋዊ እውቅና የሌለው ድርጅት በመክፈት ሰዎችን ወደ ውጭ ሀገር እልካለሁ በሚል ከተለያዩ ግለሰቦች እስከ 1 ሚሊየን 360 ሺህ ብር ድረስ በመቀበል የማጭበርበር ወንጀል ሲፈፅም እንደነበረ ፖሊስ ገልጿል።
ግለሰቡ ግንቦት 09 ቀን 2017 ዓ/ም የግል ተበዳይ ብርቱካን እመብርሀን የተባለች ግለሰብን ወደ ውጭ ሀገር እልክሻለሁ በማለት 340ሺህ ብር በመቀበልና ቼክ እንደማታለያ በመስጠት ግለሰቧንም በተባለው ቀን ወደ ውጪ ሊልክ ባለመቻሉ ለፖሊስ ሪፖርት ተደርጓል፡፡
ከግለሰቧ ክስ በተጨማሪም ሰናይት ተክላይ፣ ሠናይት ገ/ኪዳን እና አብረኀት የተባሉ ግለሰቦች ከእያንዳቸው 340ሺህ ብር በመቀበልና ወደ ውጪ ሀገር እልካችኋለሁ በማለት መሰወሩን በመግለፅ ተጨማሪ ሪፖርት ለፖሊስም ደርሶታል፡፡
የየካ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ የቀረበለትን ክስ መሰረት በማድረግ ባደረገው መረጃ የማሰባሰብ ተግባር ተጠርጣሪው ዜጎችን ወደ ውጭ ሀገር የመላክ ምንም ዓይነት ህጋዊ ፈቃድ የሌለው ከመሆኑም በተጨማሪ በተለያዩ ክ/ከተሞች በተመሳሳይ የወንጀል ድርጊት ክስ ተመስርቶበት እየተፈለገ እንደሆነም ለመረዳት ተችሏል፡፡
ግለሰቡን ሲፈለግና ሲያፈላለግ የነበረው ፖሊስም ነሐሴ 07 ቀን 2017 ዓ/ም ባደረገው ብርቱ ክትትል ተከሳሽ ይኖርበታል በተባለው ለሚኩራ ክ/ከተማ ወረዳ 14 ልዩ ቦታው የካ አባዶ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ከጠዋት 12፡00 ሠዓት ላይ በቁጥጥር ስር ሊውልም ችሏል፡፡
ፖሊስ በግለሰቡ ላይ ተጨማሪ ምርመራ የማስፋት ተግባሩን አጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን ከዚህ ቀደም በዚህ ግለሰብ ተመሳሳይ የማጭበርበር ወንጀል ተፈፅሞብኛል የሚል አካል ካለም የካ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ በአካል በመቅረብ መረጃ መስጠት የሚችል መሆኑን ማመላከቱን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በላከዉ መረጃ አስታዉቋል፡፡