የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኬይር ስታርመር እና ቮሎድሚር ዜለንስኪ በዩክሬን ሰላም በሚሰፍንበት ሁኔታ የነበራቸውን ጠንካራ የአንድነት ስሜት እና ቆራጥ አቋም ለማጽናት ከስምምነት መድረሳቸውን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በነገው ዕለት በትራምፕ እና ፑቲን መካከል ከሚካሄደው ወሳኝ ስብሰባ በፊት፣ ከፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል።
በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል የተኩስ አቁም ለማድረግ ምቹ ዕድል እንዳለ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ኬር፣ ነገር ግን የዩክሬንን የግዛት አቋም የመጠበቅ እና ዓለም አቀፍ የድንበር ህግ በኃይል መለወጥ እንደሌለባቸው ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ አጽንዖት ሰጥተዋል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ በዩክሬን ያለው ግጭት በሚቋጭበት ሁኔታ ላይ ለመወያየት በነገው ዕለት ከሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በአላስካ ይገናኛሉ።
በአላስካ ስብሰባ ላይ የማይሳተፉት ዜሌንስኪ እና ሌሎች የአውሮፓ መሪዎች፣ በትናንትናው ዕለት ከትራምፕ ጋር በጋራ የስልክ ስብሰባ በማድረግ አቋማቸውን ማረጋገጣቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
በታምራት ቢሻው