በአማራ ክልል የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ቅንጅታዊ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸዉ ተገለጸ

You are currently viewing በአማራ ክልል የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ቅንጅታዊ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸዉ ተገለጸ

AMN ነሐሴ 8/2017

በአማራ ክልል የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ቅንጅታዊ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ዓለምአንተ አግደው ገለጹ።

የክልሉ የዳኝነትና ፍትህ አካላት የትብብር መድረክ የ2017 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈፃፀምና የ2018 ዕቅድ ትውውቅ በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል።

የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት በወቅቱ እንዳመለከቱት፤ በክልሉ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የተቋማትን የትብብር መድረክ በመፍጠር የጋራ ዕቅድ ታቅዶ እየተተገበረ ይገኛል።

ፍርድ ቤትን ጨምሮ ፖሊስ፣ ፍትህ ቢሮና ማረሚያ ቤት ኮሚሽን የተካተቱበት የትብብር መድረክ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በጥምረት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ የጋራ ጉዳዮችን ተቀራርቦ በመስራት ውጤት ማምጣት መቻሉን ተናግረዋል።

ፍትህን የማስፈን ስራ ጠንካራ ቅንጅትና ትብብር እንደሚጠይቅ ጠቅሰው፤ ለዚህም የቴክኖሎጂ አቅርቦት፣ የአቅም ግንባታና የስነ ምግባር ችግሮችን በጋራ መፍታት ያስችላል ነው ያሉት።

የትብብር መድረኩ አባል ተቋማት ከፍተኛ ሪፎርም ውስጥ እንደሆኑ አንስተው፤ ይህም ማሕበረሰቡ የሚጠይቀውን የፍትህ አገልግሎት ቀልጣፋ በሆነ አግባብ ተደራሽ በማድረግ ለመመለስ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።

የዳኝነትና የፍትህ ተቋማትን ለማጠናከር በቴክኖሎጂ ታግዞ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

በክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ ሃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ታደሰ አያሌው በበኩላቸው እንዳሉት፤ የተቋማቱ የትብብር መድረክ ፍትህን በጋራ ለማስፈን ወሳኝ ስራ እያከናወነ ነው።

በዚህም የትብብር መድረኩ በፍትህ አገልግሎት ላይ ለሚስተዋሉ ተግዳሮቶች በተደራጀ አግባብ ለይቶ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት እያገዘ እንደሆነ አመልክተዋል።

ፍትህን የማስፈን ስራ የጋራ ጥረትን የሚጠይቅ እንደሆነ አንስተው፤ በስራ ሂደት የሚገጥሙ ክፍተቶችን በመሙላት የዜጎችን የፍትህ እርካታ ማረጋገጥ እንደሚያስችል አስረድተዋል።

ፖሊስ የሕዝብን እርካታ ማረጋገጥ የሚያስችል ሪፎርም እየሰራ እንደሆነም ገልጸዋል።

የህግ የበላይነትንና የዜጎችን የፍትህ እርካታ ለማረጋገጥ የትብብር መድረኩ ወሳኝ ሚና ይጫወታል ያሉት ደግሞ የክልሉ ፍትህ ቢሮ ሃላፊ ብርሃኑ ጎሽም መሆናቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በዚህም በዳኝነትና ፍትህ ተቋማት አሰራር ላይ ለውጥ በማምጣት የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥና ሰላምን ለማስፈን ድርሻው የጎላ ነው ብለዋል።

የትብብር መድረኩ እስከ ታች ያለውን መዋቅር በመፈተሽ በጥብቅ ክትትልና ድጋፍ የተሻለ የፍትህ አገልግሎት ለመስጠት የአቅም ግንባታ ስራ እንደሚከናወን ተናግረዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review