ጥበቃው አብቅቶ የ2025/26 የውድድር ዓመት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ይጀምራል።
ሻምፒዮኑ ሊቨርፑል በሜዳው አንፊልድ ምሽት 4 ሰዓት ቦርንማውዝን ያስተናግዳል ።
የመርሲሳይዱ ክለብ በመክፈቻ ጨዋታ ጥሩ ክብረወሰን አለው ። በመጨረሻዎቹ 12 የውድድር ዓመታት አንድም ጨዋታ አልተሸነፈም ። ከ12ቱ ጨዋታ 9 ሲያሸንፍ በሦስቱ አቻ ተለያይቷል ።
በኮሚኒቲ ሺልድ በክሪስታል ፓላስ ተሸንፎ ዋንጫ ያጣው ሊቨርፑል ዳግም የሊጉ አሸናፊ እንደሚሆን በርካቶች ግምታቸውን ሰጥተውታል ።
ጥራታቸው ከፍ ያሉ አራት ተጫዋቾችን ያስፈረመው ክለቡ በቀጣይም ተጨማሪ ተጫዋቾችን ያስፈርማል ተብሎ ይጠበቃል ።
ቦርንማውዝ አስቸጋሪ የዝውውር መስኮት አሳልፏል ። የአንዶኒ ኢራዮላ ተመራጭ ሦስት ተከላካዮች ክለቡን ለቀዋል ። ዲን ሃውሰን ሪያል ማድሪድን ሲቀላቀል ፣ ሚሎስ ኬርኬዝ እና ኢሊያ ዛባርኒ ለሊቨርፑል እና ፓሪሰን ዠርማ ፈርመዋል ።
ወሳኝ ተጫዋቾቹን ለመተካት አሁንም ጥረት ላይ የሚገኘው ቦርንማውዝ ከሊቨርፑል ጋር ጥሩ ክብረወሰን የለውም ። ከቀዮቹ ጋር ካደረጓቸው የመጨረሻ 12 ጨዋታዎች በ11ዱ ተሸንፈዋል ።
አንፊልድ ተጉዘው ካደረጓቸው ስድስት የመጨረሻ ጨዋታም በሙሉ ተሸንፈዋል ። በእነዚህ ጨዋታዎች 23 ግብ ተቆጥሮባቸው ሦስት ብቻ ማስቆጠር ችለዋል ።
ዛሬ ምሽትም በአንፊልድ የሚያደርጉት ጨዋታ የተለየ ውጤት ይመዘገብበታል ተብሎ አይጠበቅም ።
ከተጫዋቾች ጋር በተያያዘ ሊቨርፑል ሪያን ግራቨንበርችን በቅጣት መጠቀም አይችልም ። ኮነር ብራድሊ እና ጆ ጎሜዝ በጉዳት ምክንያት መሰላፋቸው አጠራጣሪ ነው ።
ቦርንማውዝ ጀስቲን ክላይቨርትን ጨምሮ አምስት ተጫዋቾችን በጉዳት አያሰልፍም ።
በሸዋንግዛው ግርማ