ልጆች፤ ስለ ቡሄ ጨዋታ ምን ያህል ታውቃላችሁ? አብረዋችሁ ካሉ ልጆች ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ሀሳባችሁን ተለዋወጡ፡፡ እኛ ደግሞ ያነጋገርናቸውን እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል፡፡
ናሆም ሰለሞን እባላለሁ፡፡ የምኖረው መነን አካባቢ ነው፡፡ ቡሄ ከሌሎች ልጆች ጋር ሰብሰብ ብለን የምናከብረው ስለሆነ እወደዋለሁ፡፡ ለበዓሉ እናቴ ሙልሙል ዳቦ በኮባ ጠቅልላ በመጋገር ለእኔም፣ ለጓደኞቼም ትሰጠናለች፡፡ ቡሄ ሲቃረብ አስቀድመን ዝግጅት እናደርጋለን፡፡ በዚህም በቡሄ ጭፈራ በተለየ የሚባሉትን ግጥሞች እናጠናቸዋለን፡፡ ለመጨፈሪያ የሚያገለግለንን ዱላ እናዘጋጃለን፡፡ በእለቱም ተሰባስበን በየቤቱ እንዞራለን። እንኳን አደረሳችሁ ወደምንልበት ቤት ገና ሳንገባ፣ መንገድ ስንቀሳቀስ፤ እንዲሁም ከአንዱ ቤት ወደሌላው ቤት ስንጓዝ የቡሄ ጨዋታን ግጥም እያልን ነው፡፡
ልጆችዬ ለቡሄ ጭፈራ ከሚባሉት የግጥም ስንኞች መካከል የተወሰኑትን እናካፍላችሁ፤
ቡሄ በሉ፣
ልጆች ሁሉ
ቡሄ መጣ፤
ያ መላጣ
ቅቤ ቀቡት፣ እንዳይነጣ
እነዚህን ከላይ ያሉ የግጥም ስንኞች በዜማ እያሉ ልጆች ከአንዱ ቤት ወደ ሌላኛው ይጓዛሉ፡፡ ከዚያ “እንኳን አደረሳችሁ” ወደሚሉበት ቤት ከደረሱ በኋላ ደግሞ የሚከተለውን ግጥም በዜማ ይጫወታሉ፤
መጣና በዓመቱ፤
ኧረ እንደምን ሰነበቱ፡፡
እዚህ ቤቶች እንደምን ናችሁ፤
በዓመት አንድ ቀን መጣንላችሁ፤
በዓመት አንድ ቀን የመጣ እንግዳ
እራቱ ሙክት፣ ምሳው ፍሪዳ
እነዚህን ግጥሞች በዜማ እያሉና እያሞገሱ ከጨፈሩ በኋላ፤ ብዙ ሰዎች የብር ስጦታ ይሰጧቸዋል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ሙልሙል ዳቦ ይሰጧቸዋል። የሚሰጧቸውን ብር ወይንም ሙልሙል ዳቦ ተቀብለው በግጥም እና በዜማ አመስግነው ወደሌላኛው ቤት ይጓዛሉ። ለሽልማት ወይም ለስጦታው የምስጋና ዜማ የሚከተሉትን ዓይነት ግጥሞች ይይዛል፡፡
ዓመት አውደ ዓመት
ያባብዬን ቤት
ወርቅ ይዝነብበት
እዚህ ቤት
ይግባ በረከት፡፡…
ልጆችዬ ከላይ የተገለፀውን ዓይነት የቡሄ ጨዋታ ግጥሞችን ናሆም ከጓደኞቹ ጋር በየዓመቱ ሲጫወት እንደነበር ነግሮናል። ለዘንድሮም ጥሩ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገልፆልናል። ህጻን ናሆም በዓሉ ላይ ካከናወኑት ጭፈራ በኋላ ስለሚያደርጉት ተግባር፤ “የሚሰጡንን ሙልሙል ዳቦ ተከፋፍለን እንበላለን፤ የሰበሰብነውን ገንዘብ እኩል በመከፋፈል ለትምህርት የሚያስፈልጉ ቁሳቁስ ለመግዛት እናስቀምጠዋለን” በማለት ገልፆልናል፡፡
ሌላኛው ስለቡሄ ጨዋታ አስተያየት የሰጠን ህፃን ሳሙኤል ተክሉ ነው። የቡሄን በዓል ጨዋታ በልዩ ሁኔታ እንደሚያከብረውና እንደሚወደው ይናገራል፡፡ ህጻን ሳሙኤል የቡሄ ጨዋታ አስመልክቶ ያለውን ልምድ የገለጸው፤ “ከሳምንት በፊት አባቴ ጅራፍ ይሰራልኛል፡፡ የቡሄ እለት ከሰፈር ጓደኞቼ ጋር በመሆን ጅራፉን ሳስጮህ አረፍዳለሁ፡፡ በኋላም ከጓደኞቼ ጋር በየቤቱ በመዞር ለበዓሉ የሚባሉትን ግጥሞች በማለት እንኳን አደረሳችሁ እላለሁ፡፡ በዓሉን ከጓደኞቼ ጋራ ሆኜ ማክበሬ ደስታን ይፈጥርልኛል፡፡ ወላጅ እናቴም ሙልሙል ዳቦ በመጋገር አብረው ለሚጨፍሩ፣ እንዲሁም በተለያየ ሰዓት ቤታችን እየጨፈሩ ለሚመጡት ልጆች ትሰጣለች፡፡ ዘንድሮም የቡሄ ጨዋታን ለመጫወት ከጓደኞቼ ጋር እየተዘጋጀሁ ነው” በማለት ነው፡፡
በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የፎክሎር ምሁር የሆኑት አስቴር ሙሉ (ዶ/ር) ባስተላለፉበት መልዕክት፣ “ልጆች፤ ባህሉን ያልጠበቁ ግጥሞችን መግጠምና ማዜም የለባችሁም፡፡ የገንዘብ ማግኛ እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅባችኋል” ብለዋል፡፡ እንኳን ለቡሄ በዓል አደረሳችሁ ሲሉም ለእናንተ ለልጆች መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
በለይላ መሀመድ