የጉዳፍ ጸጋይና ቢትሪስ ቺቤት የፖላንዱ ፍጥጫ

You are currently viewing የጉዳፍ ጸጋይና ቢትሪስ ቺቤት የፖላንዱ ፍጥጫ

AMN – ነሃሴ 10/2017 ዓ.ም

የ2025 ዳይመንድ ሊግ 12ኛው ከተማ ውድድር ዛሬ በፖላንድ ሲላሲያ ይካሄዳል፡፡ ከ100 ሜትር እስከ 3 ሺ ሜትር በሚደረገው የዛሬው ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለት ርቀቶች ይሳተፋሉ፡፡

የሴቶች አንድ ሺ 500 ሜትር ከዛሬ ውድድሮች ተጠባቂው ነው፡፡ በዩጂን እና ቡዳፔስት ዓለም ሻምፒዮና በአምስት እና 10 ሺ ሜትር ያሸነፈችው አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ የምትጠበቅ አትሌት ናት፡፡

የ2023 የአምስት ሺ ሜትር የዳይመንድ ሊግ አሸናፊዋ ጉዳፍ በዚህ ዓመት በቻይና ናንጂንግ የተካሄደውን የቤት ውስጥ የአንድ ሺ 500 ሜትር ስታሸንፍ ክብረወሰን ማስመዝገቧ ይታወሳል፡፡

የፓሪስ ኦሊምፒክ የአምስት እና አስር ሺ ሜትር ባለ ድሏ ቢትሪስ ቺቤት ዋነኛ የጉዳፍ ተፎካካሪ ናት፡፡ ሮም ዳይመንድ ሊግ ላይ አምስት ሺ ሜትርን በፈጣን ሰዓት ያሸነፈችው ቺቤት በምሽቱም ውድድር ትጠበቃለች ፡፡

በርቀቱ የማሸነፍ ታሪክ ያላቸው ኢትዮጵያውያኑ ብርቄ ኃየሎም ፣ ፍሬወይኒ ኃይሉና ወርቅነሽ መሰለም ቀላል ግምት አልተሰጣቸውም፡፡ የርቀቱ የነጥብ መሪ አየርላንዳዊቷ ሳራህ ሂሊ፣ ስፔናዊቷ ማርታ ፔሬዝ፣ አሜሪካዊቷ ማክሊን ሂተር እንዲሁም አውስትራሊያዊቷ ሳራህ ቢሊንግስ ሌሎች በዛሬው ሩጫ የሚጠበቁ አትሌቶች ናቸው፡፡

የሴቶች ሶስት ሺ ሜትር ሌላው ኢትዮጵውያን የሚሳተፉበት ርቀት ነው፡፡ ልቅና አምባው፣ አለሺኝ ባወቀ፣ ማርታ አማየሁ፣ መቅደስ አለምሸትና አክሱማዊት ኢምባዬ ይሳተፋሉ፡፡

ኬንያዊቷ ፌይዝ ኪፕየጎን ርቀቱን ለማሸነፍ ቀዳሚውን ግምት ያገኘች አትሌት ናት፡፡ ኡጋንዳዊቷ ቻሪቲ ቼሮፕ እና አውስትራሊያዊቷ ጄሲካ ሁል ሌሎች የሚጠበቁ አትሌቶች ናቸው፡፡

በታምራት አበራ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review