ትራምፕ ዩክሬን የሩሲያን የሰላም ስምምነት እንድትቀበል ጠየቁ

You are currently viewing ትራምፕ ዩክሬን የሩሲያን የሰላም ስምምነት እንድትቀበል ጠየቁ

AMN- ነሐሴ 11/2017 ዓ.ም

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት የተኩስ አቁም ላይ ያላቸውን አቋም ቀይረው፣ ዩክሬን ሩሲያ ያቀረበችውን የሰላም ስምምነት እንድትቀበል ጠይቀዋል፡፡

ትራምፕ ከሩሲያ አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር ከተገናኙ በኋላ፣ ወደ ቋሚ የሰላም ስምምነት ለመሸጋገር ዩክሬን የሩሲያን የሰላም ስምምነት እንድትቀበል መጠየቃቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

አርብ ያደረጉትን ስብሰባ ተከትሎ፣ ትራምኘ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ “በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ያለውን ጦርነት ለማስቆም የተሻለው መንገድ ይህ ነው” ብለዋል።

ትራምፕ በነገው ዕለት የዩክሬኑን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪን በዋሽንግተን እንደሚቀበሉ እና የሰላም ስምምነቱን እንዲቀበሉ እንደሚያሳስቧቸው ዘገባው ገልጿል።

ከጉባኤው በኋላ ከትራምፕ ጋር የተደረገውን የስልክ ውይይት ተከትሎ፣ ዜለንስኪ እውነተኛና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ጥሪ ማድረጋቸውን እና መገዳደል መቆም አለበት ሲሉ መናገራቸውም ተሰምቷል።

ትራምፕ ከአውሮፓ መሪዎች ጋር በነበራቸው ውይይት የዩክሬን ዋና ፍላጎት በዘላቂ ሰላም ስምምነት ዙሪያ ንግግር ከመደረጉ በፊት፣ አፋጣኝ የተኩስ አቁም ላይ መድረስ እንደሆነ መነጋገራቸው ይታወሳል።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት፣ በሁለቱ ሀገራት መካከል ዘላቂ ሰላም ለማስፈን፣ የግዛቶች ልውውጥ እንደሚኖር ገልፀው እንደነበርም ዘገባው አስታውሷል።

ከቀናቶች በፊት የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት፣ ሩስያ ጥቃቶችን ለማድረስ እንደ መንደርደሪያ ልትጠቀምበት ስለምትችል ሎሃንስክ እና ዶኔስክን ያቀፈውን የዶንባስ ግዛት እንድትቆጣጠር እንደማይፈልጉ ማስታወቃቸውም ተመላክቷል።

በብርሃኑ ወርቅነህ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review