በቀጣይ ሁለት ወራት በሲዳማ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ የዝናብ ስርጭት ሊኖር እንደሚችል የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢኒስቲትዩት አስታወቀ።
ድንገተኛ ጎርፍና የመሬት መንሸራተት አደጋ ሊከሰት ስለሚችልም ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም ተመላክቷል።
በኢንስቲትዩቱ የሲዳማ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሎች መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ከፍያለው አየለ እንደገለጹት፣ በክልሎቹ እስከ መጪው ጥቅምት ወር ድረስ መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ሊመዘገብ ይችላል።

አብዛኛው የሲዳማ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች እንዲሁም የደቡብ ኢትዮጵያ ደጋማ አካባቢዎች የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ መሆናቸውን አስታውሰዋል።
የተቀሩት የደቡብ ኢትዮጵያ ቆላማ አካባቢዎች ደረቃማ ሆነው እንደሚቆዩ የጠቆሙት አቶ ከፍያለው፣ በእነዚህ ክልሎች የክረምቱ ዝናብ መደበኛና ከመደበኛ በላይ እንደሚሆንም ጠቁመዋል።
በቀሩ የክረምት ወራት ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚጠበቅ የሚቲዎሮሎጂ ትንበያው ያሳያል ያሉት አቶ ከፍያለው፣ በዚህም በክልሉ ተዳፋታማ በሆኑ ቦታዎች፣ በወንዝ ዳር አካባቢዎችና በታችኛው የሐይቆች ተፋሰስ ድንገተኛ ጎርፍ እና በማሳ ላይ ውሃ መተኛ የሚጠበቁ ክስተቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።
የሲዳማ ክልል አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አበራ ዊላ በበኩላቸው እንዳሉት የክረምት ዝናብን ተከትሎ የሚያጋጥሙ ክስተቶችን ለመከላከል ኮሚሽኑ ከኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት ጋር ተቀራርቦ እየሰራ ይገኛል።

በየጊዜው የሚቲዎሮሎጂ መረጃን መሰረት በማድረግ በክልሉ በአራት ዞኖች ካሉ 36 መዋቅሮች ጋር ድንገተኛ የጎርፍ አደጋ ቢያጋጥም ጉዳት እንዳይደርስ ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
አምና በክረምት ወቅት በነበረው ሀይለኛ ዝናብ በክልሉ ወንሾ ወረዳ የመሬት መንሸራተት አደጋ አጋጥሞ እንደነበር ያስታወሱት ኮሚሽነሩ፣ በዚህም የሰው ህይወት ከማለፉ ባለፈ በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል ብለዋል።
ዘንድሮ መሰል ችግሮችን ቀድሞ ለመከላከል በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ኮሚሽነር አበራ መግለጻቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ህብረተሰቡ በክረምቱ እየጣለ ያለውን ዝናብ ተከትሎ ሊከሰት በሚችል ድንገተኛ የጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት አደጋ ለችግር እንዳይጋለጥ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበትም አሳስቧል።