መንግስት የሠራተኛውን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ከመስከረም 2018 ዓ.ም ጀምሮ የደሞዝ ማሻሻያ ለማድረግ ያስተላለፈው ውሳኔ፣ የሠራተኛውን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የሚያግዝ በጎ ተግባርና አዎንታዊ እርምጃ መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
የደሞዝ ማሻሻያው ከሀገሪቱ ጠቅላላ ህዝብ ቁጥር ከ2 በመቶ የማይበልጠውን የመንግስት ሠራተኛ የኑሮ ሁኔታ በማሻሻል መንግስት ለህብረተሰቡ የሚሰጠው አገልግሎት ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን ታስቦ የተደረገ መሆኑ ይታወቃል ብለዋል፡፡
ከዚህ በፊት ካለው ልምድ ለመገንዘብ እንደሚቻለው አብዛኛው የንግዱ ማህበረሰብ ሕግና ስርዓትን ጠብቆ የሚሠራ መሆኑ የሚያስመሰግን ቢሆንም፣ የተወሰኑ በአፍቅሮተ-ነዋይ የታወሩ ነጋዴዎች ለሠራተኛው ኑሮ ማሻሻያ የሚደረገውን የደሞዝ ጭማሪ ምክንያት በማድረግ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት መሯሯጥ ተስተውሏል ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡
እንደዚህ አይነት ኢ-ሞራላዊ ያልተገባ ጥቅም ማግኛ ሩጫ ከንግድ ሥነ-ምግባርና ሞራል አኳያ ሲታይ አሳፋሪ ተግባር መሆኑ ታውቆ፣ በአዋጅ ቁጥር 980/2008 እና 813 /2006 እንዲሁም በወንጀል ሕግ 1996 ተላልፎ ህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ በማድረግ በማንኛውም የንግድ እቃ እና አገልግሎት ግብይት ላይ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ወይም ሰው ሰራሽ እጥረት ለመፍጠር ምርት የሚሰውሩ እና አላግባብ የሚያከማቹ ሕገ-ወጥ ነጋዴዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ሚኒስትሩ አሳስበዋል፡፡
በየደረጃው የሚገኝ የንግድ መዋቅር ከሚመለከታቸው የፍትህ እና ፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የተጠናከረ የገበያ ማረጋጋት፣ የክትትልና ቁጥጥር ሥራ በማጠናከር፣ በአጥፊዎች ላይ አስተማሪ እርምጃ እየተወሰደ የግብይት ሂደቱ በተረጋጋ ሁኔታ እንዲቀጥል እንዲደረግም አስታውቀዋል፡፡
በአስማረ መኮንን