ኢየሱስ ክርስቶስ ለሀዋርያቱ መለኮቱን በገለጠበት ዕለት ጊዜው ምሽት ነበር፡፡እረኞችም ከብርሃኑ ድምቀት የተነሣ እየተገረሙና እየተደነቁ ወደ ቤት አልተመለሱም፡፡ በልጆቻቸው መዘግየት የተዳናገጡ ወላጆች ችቦ አብርተውና ዳቦ ይዘው ፍለጋ ወጡ፡፡
ይህ ክንውን ከዘመናት በፊት የተፈጸመ ቢሆንም በኢትዮጰያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና በምዕመኑ ዘንድ የሚከበር በዓል ነው።
«ቡሄ» ለሚሉ ልጆች ሙልሙል ዳቦ የሚሰጠውና ችቦ በማብራት በዓሉ የሚከበረው ከዚህ በመነሣት ነው፡፡
ከዚያን ግዜ ጀምሮ በገጠርም ሆነ በየከተማው ልጆች ጅራፋቸውን ገምደው ሲያጮሁ ይሰነብታሉ።
እናቶችም ለበዓሉ ዝግጅት ስንዴ ሲለቅሙ፣ ሲፈትጉ፣ ሲፈጩ ይሰነብታሉ።
በዓሉ የሚከበረው ከዋዜማው ጀምሮ የሠፈር ልጆች በየቤቱ እየዞሩ ሆያ ሆዬ እና አሲዮ ቤሌማ እያሉ ይጨፍራሉ።
ቡሄ በሉ (2)
ኢትዮጵዊያን ሆ፣
ታሪክ አላችሁ ሆ፣
ባህላችሁን ያዙ
አጥብቃችሁ ሆ!
ችቦውን አብሩት ሆ፣
እንደ አባቶቻችሁ ሆ፣
ሚስጢር ስላለው ሆ፣
ደስ ይበልስችሁ ሆ!
አባቶቻችን ሆ፣
ያወረሱን ሆ፣
የቡሄን ትርጉም ሆ፣
ያስተማሩን ሆ፣
እንድንጠብቀው ሆ፣
ለኛ የሰጡን ሆ፣
ይህን ነውና ሆ፣ ያስረከቡን ሆ …………………..
እያሉ ከጨፈሩ በኋላ በሰፈር ልጅ በመቧደን በአለቆቻቸው መሪነት ተስማምተው የእግር አጠባ፣ የመነጣጠቅ ጨዋታ፣ የገበጣ ጨዋታ፣ ፈረስ ግልቢያና የውሃ መራጨት እንዲሁም የነጻ ትግል ውድድር ያካሂዳሉ።
ከአራቱ ወቅቶች መካከል ክረምት ጭጋጋማ እና ደመናማ ነው፡፡
ይህ የክረምቱ፣ ጭጋግ እና ደመና ተወግዶ የብርሃን ወገግታ መታየት የሚጀምረው ከደብረ ታቦር በኋላ ስለሆነ ነው መላጣ፣ ገላጣ የተባለው።
ልጆች ሙልሙል ዳቦ ተጋግሮ እስኪጠግቡ በወተት የሚበሉበት፣ እረኞች ከሆኑ ከከብቶች ጥበቃ ነጻ የሚሆኑበት፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ሙልሙላቸውን ይዘው ከብቶቻቸውን የሚያሰማሩበት ነው፡፡
የቡሄ ዕለት ማታ በየቤቱ፣ በየአብያተ ክርስቲያናቱ እና በየአድባራቱ ችቦ ይበራል፣ ይህም በደብረ ታቦር ለታየው ብርሃነ መለኮት ምሳሌ እንደሆነ ይነገራል፡፡
ችቦ መብራቱም ወላጆች ለልጆቻቸው ስንቅ ይዘው ሲሄዱ ችቦ አብርተው እንደሄዱ ማሳያ እንደሆነም ይታመናል፡፡
ቡሄ፣ በሀገራችን ከሚገኙ የተለያዩ ሃይማኖታዊ በዓላት መካከል ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ የመጣ ሀይማኖታዊ በዓል ነው።
በአለኸኝ አዘነ