መለኮት የተገለጠበት የደብረ ታቦር (የቡሄ) በዓል

You are currently viewing መለኮት የተገለጠበት የደብረ ታቦር (የቡሄ) በዓል
  • Post category:በዓል

‎ቡሄ በሉ! ሆ!

‎ልጆች ሁሉ! ሆ!

‎የኛማ ጌታ፣ የዓለም ፈጣሪ

‎የሰላም አምላክ፣ ትሁት መኻሪ

‎ድምፅህን ሰማና በብሩህ ደመና

‎የቡሄው ብርሀን ለኛ በራልን….

‎ይህ ስንኝ በኦርቶዶክ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ መሰረት ኢየሱስ ክርስቶት በደብረ ታቦር ተራራ ለሶስቱ ደቀ መዛሙርቶች መለኮትነቱን የገለጠበት እንደሆነ ይታመናል።

‎ይህም ማለት ኢየሱስ ክርስቶስ ሦስት ደቀመዛሙርቱን ይዞ ወደ ተራራው የወጣበትና ፊቱ እንደ ፀሐይ የበራበት ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ የሆነበት ቦታ ነው፡፡

‎ይህ ስፍራ ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበት ተራራ መሆኑን ነው ጥንታዊቷ ቤተክርስቲያን የምታስተምረው።

‎በአስተምህሮቱ መሰረት ኢየሱስ ክርስቶስ በመለኮትነት ሲለወጥ ከሰማይ “እግዜአብሔር አብ ” የምወደው ልጄ እርሱ ነው። እሱን ስሙት “ብሎ የተናገረበትን ተወስዶ በጥኡመ ዝማሬ ( ወረብ ) መዘጋጀቱ ይነገራል።

‎በዚህ መሰረት ቤተክርስቲያኗ ከምታከብራቸው ሃይማኖታዊ ትውፊት ካላቸው በዓላት ውስጥ በየዓመቱ ነሐሴ 13 ቀን የሚከበረው ደብረ ታቦር ወይም የቡሄ በዓል አንዱ ነው፡፡

‎የዚህን በዓል አስተምህሮ እና ታሪካዊ ዳራ በተመለከተ ኤ ኤም ኤን የኢትዮጰያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አባቶችን እንደሚከተለው አነጋግሯል።

‎የደብረ ብስራት ቅዱስ ገብረኤል ቤተክርስትያን ዋና አስተዳዳሪ መላከ ገነት መዝገቡ ላቀው ስለ ደብረ ታቦር ሲያስረዱ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ሶስቱን ሀዋርያት ወደ ደብረ ታቦር ተራራ ይዟቸው ከወጣ በኃላ ወደ ብርሀነ መለኮት ሆኖ የታየበት እንደሆነ ያስረዳሉ።

‎ቤተክርስቲያኗ የታቦር ተራራን በተለያዩ ምሳሌዎች እንደምትገልፃቸው ዋና አስተዳዳሪው ገልፀው፣ ተራራው የወንጌል፣ የመንግስተ ሰማያት፣ የቤተክርስቲያን ምሳሌዎች እንደሆኑ ታስተምራለች ብለዋል።

‎የደብረ ታቦር በዓል ቤተክርስቲያኗ በድምቀት ከምታከብራቸው በዓላት ውስጥ የሚጠቀስ ሲሆን፣ በገጠራማው የአገራችን ክፍል ታዳጊዎች በበዓሉ ዋዜማ ተራራ ላይ በመውጣት ጅራፍ የሚያስጮሁበት የግርማ መለኮቱ ማሳያ መሆኑን አስረድተዋል።

‎ከዚህ በተጨማሪ በማህበረሰቡ የበዓሉ መድረሱን የሚነግሩበት ስነ ግጥም እንዳላቸው፣ “ዶሮ ከጮኸ የለም ለሊት፣ ቡሄ ካለፈ የለም ክረምት” እየተባለ የሚነገርለት በዓለ ወቅት ነው ይላሉ።

‎የቀጨኔ ደብረሰላም መድሀኒዓለም እና ደብረ ትጉሀን ቅዱስ ገብርኤል አብያተክርስቲያን ዋና አስተዳዳሪ መላከ ሰላም አምደ ወርቅ ደሴ በበኩላቸው፣ የደብረ ታቦር በዓል ድርጊቱ በተከናወነበት የሚጠራ በዓል መሆኑን ያስረዳሉ።

‎በደብረ ታቦር ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሀነ መለኮቱን የገለጠበት ተራራ መሆኑን ጠቅሰዋው፣ የበዓሉ አንድምታ የመለኮት መገለጥን የሚያመለክት ነው ብለዋል።

‎ከሀይማኖታዊ የበዓል ስረዓቱ እንዳለ ሆኖ በምዕመኑ ዘንድ ከዋዜማ ጀምሮ ሙልሙል በመጋገር ችቦ በማብራት በዓሉን በድምቀት ያከብራሉ።

‎ታዳጊ ወንዶችም በአገር ልብስ ተውበው እና አሸብርቀው በየቀዬው እየዞሩ ቡሔ በሉ … ቡሔ በሉ … እያሉ እያዜሙ በዓሉን በድምቀት ያከብራሉ።

‎በሔለን ተስፋዬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review