አርቲስት ደበበ እሸቱ ለኢትዮጵያ የኪነ ጥበብ ዘርፍ ትልቅ አሻራ አሳርፏል ሲሉ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ገለጹ፡፡
የአንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ አስከሬን የክብር ሽኝት በብሔራዊ ቴአትር እየተካሄደ ነው።
በሽኝት መርሐ ግብሩ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች፣ ቤተሰቦቹ፣ ወዳጅ ዘመዶቹ፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ፣የስራ አጋሮቹ እንዲሁም አድናቂዎች ተገኝተዋል።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቲያትር የአርቲስት ደበበ እሸቱ የስነፅሑፍ ስራዎች እየተዘከሩና የህይወት ታሪኩ እየቀረበ ሲሆን በአርቲስቱ ህልፈት በርካቶች ሀዘናቸውን እየገለፁ ይገኛሉ።
በሽኝት መርሐግብሩ ላይ የተገኙት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፤ አርቲስቱ በዘመኑ ለኢትዮጵያ የኪነ ጥበብ ዘርፍ ትልቅ አሻራን አሳርፏል ብለዋል።
ሚኒስትሯ ከራስ ጥቅም ይልቅ ለሀገር ፍቅርና አንድነት ከፊት የቆመ በመሆኑ በስራዎቹ ሀገር ሁሌም ትዘክረዋለች ብለዋል።
የአንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ ሥርዓተ ቀብር በዛሬው ዕለት 8:00 ላይ በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ይፈጸማል።
በኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ ዘርፍ የላቀ አስተዋጽኦ ያበረከተው አንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ ባደረበት ሕመም በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ ከትናንት በስቲያ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።
በደሳለኝ ሞሐመድ