እያደገ የመጣው የቻይና የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እና ያቀደችው ወታደራዊ ትርኢት

You are currently viewing እያደገ የመጣው የቻይና የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እና ያቀደችው ወታደራዊ ትርኢት

AMN – ነሐሴ 14/2017 ዓ.ም

ቻይና ከተለመደው ወታደራዊ ግንባታዋ ጎን ለጎን የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎቿን በፍጥነት እያሰፋች ነው፡፡

ለዚህም እንደ ምክንያትነት የፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ በ2027 ታይዋንን የማጠቃለል ቅድመ ዝግጅት ትዕዛዝ እንደሚጠቀስ ሮይተርስ አስንብቧል፡፡

ይህም የቻይናን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ በየብስ፣ በአየር እና በባህር ላይ የማምጠቅ አቅምን ሊጨምር እንደሚችል የአሜሪካ ባለስልጣናት ጠቁመዋል፡፡

ምንም እንኳን ቻይና ኒውክሌር መሳሪያን ቀድማ ያለመጠቀም ፖሊሲ እንዳላትና ስትራቴጂዋ ሙሉ በሙሉ ራስን በመከላከል ላይ ያተኮረ እንደሆነ ብታስታውቅም፣ የኒውክሌር ሃይሎቿ ለአደጋ ከተጋለጡ እና ከታይዋን ጋር በተያያዘ ህልውናዋን አደጋ ላይ የሚጥል ከሆነ ቀድማ ልትጠቀመው እንደምትችል እንደሚያምን ፔንታጎን ባሳለፍነው አመት ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል፡፡

የቻይና የመከላከያ ሚኒስትር ግን አስተያየቱን አለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማሳሳት ያለመ ነው በሚል ውድቅ አድርጓል፡፡

በተያያዘም ቻይና የሁለተኛውን የዓለም ጦርነት ማብቃት 80ኛ ዓመት ለመዘከር በመጪው ወር በቤጂንግ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ትርኢት እንደምታካሂድ አስታውቃለች፡፡

በወታደራዊ ትርኢቱን በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሚታደሙት ሲሆን የላቁ የምትላቸውን የጦር መሳሪያዎቿን እና ወታደራዊ አቅሟን የምታሳይበት እንደሚሆን ይጠበቃል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል፡፡

በትርኢቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ የጦር ጀቶች፣ እግጅ ፈጣን የተባሉ ሚሳኤሎች እንዲሁም ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን ለእይታ በማብቃት ወታደራዊ ሃይሏ የደረሰበትን ዘመናዊነት ፍንጭ የምትሰጥበት እንደሚሆን የቻይና ወታደራዊ ባለስልጣናት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

በ2ኛው የአለም ጦርነት የጃፓንን እጅ መስጠት በሚዘክሩበት በዚህ ትርኢት፤ ከሚቀርቡት መሳሪያዎች መካከል አብዛኛዎቹ ለህዝብ ይፋ ሲደረጉ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሚሆንም ተመላክቷል፡፡

ለመስከረም 3 የታቀደውና የ70 ደቂቃዎች ርዝማኔ የሚኖረው ወታደራዊ ትርኢቱ፣ ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ እና የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድመር ፑቲንን ጨምሮ የውጭ ሃገራት መሪዎች በተገኙበት እንደሚካሄድ ተዘግቧል፡፡

ከዚህ በፊት በፈረንጆቹ 2015 ቻይና ባካሄደችው ወታደራዊ ትርኢት፣ የጃፓንን ጨምሮ በርካታ የጎረቤት ሃገራት መሪዎችን ብትጋብዝም፣ ትርኢቱ ወታደራዊ ሃይሏን ለማሳየት የምትጠቀምበት ነው በሚል ግብዣውን ውድቅ በማድረግ ትርኢቱን አለመታደማቸውን ዘገባው አስታውሷል፡፡

በሊያት ካሳሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review