ለኢትዮጵያ እንደ ሀገር ወደኋላ መቅረት ምክንያቱ ሀገራዊ አቅሞች መዳከም ናቸው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመደመር ሀሳብ ላይ የጻፉት አራተኛውንና “የመደመር መንግሥት” የተሰኘውን አዲስ መጽሐፍ አስመልክቶ በነበራቸዉ ቆይታ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ወደኋላ ስላስቀራት ጉዳይ አብራርተዋል፡፡
ከዓለም ጋር ጎን ለጎን እየተጓዝን ሳለ ሌላው ዓለም ፈጥኖ እኛ ወደኋላ የቀረንበት ጉዳይ በአጭሩ ወደኋላ መንሸራተት ወይም ደግሞ ከሌላው ባነሰ ፍጥነት መጓዝ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል፡፡
አንዱ በፍጥነት እየተጓዘ እኛ በዝግታ የምንጓዝ ከሆነ በመካከላችን ያለው ክፍተት እየሰፋ እንዲሄድ ምክንያት ይሆናል ብለዋል፡፡
ይህንን ሁኔታ የመደመር መንግስት በእንግሊዝኛው ምህፃረ ቃል (አይ ሲ ኢ) ይለዋል በማለትም ገልጸዋል፡፡
ይህም የተቋማት፣ የባህል እና የኢኮኖሚ መዳከም እንደሆነ አንስተዋል፡፡
ከተቋማት መዳከም ጋር በተገናኘም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት መቶ ዓመታት ሦስት ገደማ ሥርዓቶች እንደነበሩ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አንዱ ሥርዓት ሲወድቅ፣ የመጣው ለውጥ ዋነኛ ሥራው ያለፈውን ሥርዓት ተቋማት ማፍረስ እንደነበርም በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡
ይህን መሰሉ አካሄድም የተቋማት ቅቡልነትን እንዳሳጣዉ ነው ያመላከቱት፡፡
የባህል መዳከምን በተመለከተ ሲያነሱም፣ የኢትዮጵያ ህዝብ አስደናቂ ባህሎች ያሉት ቢሆንም፣ አሁን ግን ስራ የማይሰሩ፣ ሥራ የማያሰሩ፣ ሥራ የሚሰሩ ሰዎች የሚሳደቡ፣ ዕውቀት የሚጠሉ፣ ምንም መልካም ነገር ቢያዩ ማድነቅ የሚተናነቃቸው እና ለመደማመጥ ቦታ የሌላቸው ሰዎች እየተበራከቱ መጥተዋል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ሌላው የኢኮኖሚ ድቀት መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ በሌሎች የዓለም ሀገራት ኢንደስትሪያላይዜሽን ከ200 ዓመታት በፊት መጀመሩን በመጥቀስ፣ ኢትዮጵያ ግን ከ200 ዓመታት በኋላ ገና ግብርናን ለማዘመን ማሽን እየጠየቀች መሆኗን አንስተዋል፡፡
በድምሩ ተቋማዊ፣ የባህላዊ እና ኢኮኖሚያዊ ድቀቶች አንዱ አንዱን የሚከተል በመሆኑ፣ አንደኛው ሲቀንስ አንዱን ይዞ እንደሚሄድ በማንሳት፣ ይህም ኢትዮጵያን ወደኋላ እንድትቀር እንዳደረጋት ገልጸዋል፡፡
በታምራት ቢሻው