ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እንደ ሃገር እየተከናወኑ ባሉ የከተማ እና የገጠር ኮሪደር ልማት ስራዎች ዙሪያ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
መንግስት ከተሞችን ለማልማት ገና ከምርጫ በፊት አስቀድሞ ቃል መግባቱን አንስተዋል።
አዲስ አበባን እንደ ስሟ አበባ ለማድረግ በታቀደዉ መሰረት ሰፋፊ ስራዎች መሰራታቸውን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰው ልጆችን ኑሮ ምቹ ማድረግ : አገልግሎትን ማቅለል ነገሮችን በተሻለ መንገድ ማቅረብና ማሟላት መሆኑን በመገንዘብ የከተሜነትን የኑሮ ዘዬ ለማስፋፋት እየተሰራ ነው: በዚህም ውጤት ተገኝቷል ብለዋል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተሞች የማህበራዊ : ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ማዕከል ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስርአት ያለው ህብራዊ አንድነት መገለጫ በመሆናቸው ከፍተኛ ኢኮኖሚ ይንቀሳቀስባቸዋል ብለዋል።
ስራ ፈጠራ ይስፋፋባቸዋል ባጠቃላይ የላቀ ዕድገት እና የፈጠራ አንቀሳቃሽ ሞተር መሆናቸውን ነው የገለፁት ፡፡
ከተሜነት የጤናማነት የዘመናዊ አኗኗር ዘዬ መገለጫ መሆናቸውን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደ መንግስት ከተማን ወደ ጎን በመተው በነጠላ ስራ ብቻ በማሰብ ብልፅግናን ማረጋገጥ አይቻልም ነው ያሉት።
ብልፅግና ከተማን ብቻ እያለማ ገጠርን የሚተው አይደለም በሁለቱም ጥሩ እና ውጤታማ ስራ እየተሰራ ነዉ ብለዋል።
በቅረቡ የሚመረቀው በማዕከላዊ ኢትዮጵያ የተጀመረው የገጠር ኮሪደር ልማት የሚያስደምም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአርሶ አደሩን ህይወት በብዙ የሚያዘምንና የሚያሻሽል ነው ይህም መንግስት ገጠርንም ያካተተ ዘላቂነት ያለው ሰራ እየሰራ ለመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል ፡፡
በአዲስ አበባ እና በሃገሪቱ በተለያዩ ከተሞች እና የገጠር አካባቢዎች የኮሪደር ልማት ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እስካሁን በተሰሩ ስራዎች እንደ አዲስ አበባ ብቻ ያማረ አስፋልት እና የእግረኛ መንገድ ብቻ ሳይሆን ወጣቶች የስራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችሏል ብለዋል።
በተጨማሪም ዜጎች ንፁህ እና ምቹ በሆነ አካባቢ እንዲኖሩ ከማስቻሉ በላይ የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ ስራዎች በመሰራታቸው ውጤት ተመዝግቧል ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ነው የገለፁት።
በያለው ጌታነህ