መንግስት ሌብነትን ለመከላከል ጠንካራ ሥራ በመስራት ላይ እንደሚገኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለፁ

You are currently viewing መንግስት ሌብነትን ለመከላከል ጠንካራ ሥራ በመስራት ላይ እንደሚገኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለፁ

AMN- ነሐሴ 14/2017 ዓ.ም

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመደመር መንግስት በሚል በፃፉት አዲሱ መፅሀፍ ዙርያ በሰጡት ማብራሪያ፣ መንግስት ሌብነትን ለመከላከል ጠንካራ ሥራ በመስራት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ሌብነት ብዙ መልክ አለው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የሥራ ኃላፊዎች በተለያዩ የሥራ ዘርፍ ላይ ለሚሰጠው አገግሎት ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት የሚፈፅሙት አንደኛው መሆኑን አንስተዋል።

ሌብነት በቀጥታ ከመንግስት ጋር ብቻ እንደማይተሳሰር ያስገነዘቡ ሲሆን፣ በተለያዩ ዘርፎች ባሉ አካላትም እንደሚንፀባረቅ ገልፀዋል።

የመደመር መንግስት የዚህ አይነቱን ሌብነት እንደ አረም እንደሚገልጸውም ነው ያነሱት።

አረሙን መለየት ከተቻለ መንቀሉ ቀላል ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።

ይሁንና የዚህ አይነቱን ሙስና ከባድ የሚያደርገው፣ ከተክሉ ጋር የመመሳሰሉ እና የመብዛቱ ጉዳይ ነው ብለዋል።

ሁለተኛው በግለሰቦችና በቡድኖች መካከል በተቀናጀና በተደራጀ መልኩ የሚፈፀም ከበድ ያለ ሙስና ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከበድ ያለው ሙስና ሥልጣን፣ ሚዲያ እና የጦር መሳሪያን በያዙ ሰዎች ይፈፀማል ብለዋል።

መንግስታት ሳይበሩ እነዚህ አካላት ሙስና ሲፈፅሙ ቢያዩ ወዲያው ለመንቀል ይቸገራሉ ሲሉ ገልፀዋል።

በበርካታ የዓለም ሀገራት የሚፈፀም ሙስና መኖሩን ያመላከቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ በኢትዮጵያም ከለውጡ በፊት ባለሥልጣናት ከባለሀብት ጋር ተመሳጥረው ህግና ፖሊሲ እስከ ማውጣት የሚደርሱበትና ያሻቸውንም የሚያደርጉበት የሙስና አካሄድ እንደነበር ገልጸዋል።

ይሁንና መንግስት ሌብነትን ለመከላከል በሰራው ጠንካራ ሥራ፣ ሥልጣን ተጠቅመው ከግል ባለሀብት ጋር በመመሳጠር ፖሊሲ እስከማውጣት የሚደርስ ሙስና አለመኖሩን አመላክተዋል።

እንደ ዋርካ የሚገለፅ ከበድ ያለ ሙስና ባይኖርም፣ እንደ አረም የሚገለፅ ሌብነት በስፋት እንደሚስተዋል አንስተዋል።

የመደመር መንግስት እንደ አረም የተስፋፋውን ሌብነት የሚከላከለው አረሞቹን በመለየት እና ከንክኪ ነፃ የሆነ ሥርዓት በማበጀት እንደሆነም አስታውቀዋል።

ከዚህ አንፃር መንግስት የጀመረውን የመሶብ አገልግሎት በአብነት ጠቅሰው በቀጣይም በተለያዩ የክልል ከተሞች አግልግሎቱ እንደሚስፋፋ ተናግረዋል።

በማሬ ቃጦ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review