የመንግስት እና የህዝብ አጋርነት አዲስ እሳቤ ሀገርን የሚያሻግሩ ስራዎች ማከናወን እንደሚያስችል በግልጽ ያሳየ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ

You are currently viewing የመንግስት እና የህዝብ አጋርነት አዲስ እሳቤ ሀገርን የሚያሻግሩ ስራዎች ማከናወን እንደሚያስችል በግልጽ ያሳየ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ

AMN ነሐሴ 14/2017

የመንግስት እና የህዝብ አጋርነት ጽንሰ ሀሳብ ሀገርን የሚያሻግሩ ውጤታማ ስራዎች ማከናወን እንደሚያስችል በግልጽ የሚያመላክት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመደመር ሐሳብ ላይ የጻፉት አራተኛውንና “የመደመር መንግሥት” የተሰኘውን አዲስ መጽሐፍ በተመለከተ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ቃለ መጠይቅ አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ብዙ ጊዜ ስራዎች የሚከናወኑት በመንግስት እና በግሉ ዘርፍ ብቻ ወይም በመንግስትና የግል አጋርነት መሆኑን ገልጸዋል።

መንግስት ከግሉ ዘርፍ ጋር በአጋርነት ከሚያከናውነው ስራ በመሻገር የመንግስትና የህዝብ አጋርነት መፍጠሩን አመልክተዋል።

የወንዝ ዳር ልማት ፕሮጀክት አብዛኛው ገንዘብ የተገኘው ከማህበረሰቡ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፕሮጀክቱን የጉልበት ስራ ያከናወነው ማህበረሰቡ እንደሆነ ተናግረዋል።

ዜጎች ችግኝ በመትከል፣ በኮሪደር ልማት፣ ሀገርን በማስዋብ፣ በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ትምህርት ቤቶችን የመገንባትና የማደስ ስራ ህዝቡ ሰፊውን ድርሻ እንደሚይዝ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት።

ይህም ከመንግስትና የግል አጋርነት አልፎ መንግስትና ህዝብ የጋራ ራዕይ ሰንቀው ከሰሩ ሀገርን የሚያሻግሩ ውጤታማ ስራዎችን ማከናወን እንደሚችሉ የሚያመላክት መሆኑን ተናግረዋል።

የመንግስት እና የህዝብ አጋርነት ከመደመር እሳቤና ከመደመር መንግስት ውጥኖች ጋር የተጋመደ ነው ብለዋል።

በቀጣይም መንግስት ከህዝብ ጋር በጋራ በመሆን ባከናወናቸው ስራዎች ያገኛቸውን ውጤቶች በተጠናከረ መልኩ እንደሚያስቀጥል ገልጸዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review