ፍራንክ ካፓሪዮ ይባላሉ፡፡ ለአራት አስርተ አመታ በዳኝነት ስራ ላይ አገልግለዋል፡፡
አዛውንቱ ዳኛ በ2023 ጡረታ ከመውጣታቸው በፊት ለአመታት ከባድ የሆነውን የዳኝነት ስራ በፈገግታ እና በርህራሄ ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡
ፍራንክ፣ በአንድ ችሎት ላይ ፈገግታ በሞላው ፊት ውሳኔን ሲሰጡ ተቀርጾ የተሰራጨው እና በማህበራዊ ትስስር ገጽ ከቢሊየን በላይ ጊዜ የታየው ተንቀሳቃሽ ምስል “የአለም ምርጡ ዳኛ” የሚል ስያሜን አስገኝቶላቸውል፡፡
የትራፊክ ቅጣት፣ ፍትሀዊ ባልሆነ መንገድ ከመኖሪያ ቤት መሰናበት፣ እና ሌሎችም ማህበራዊ ጉዳዮችን የሚዳኙት “ሩህሩሁ ዳኛ” ከሳሽ እና ተከሳሽን በፈገግታ እየተመለከቱ አንዳንድ ጊዜም እንደ ጓደኛ እየሳቁ በማናገር ፍርድ ሲሰጡ በተደጋጋሚ ተስተውለዋል፡፡
በደግነት የተሞላ ነው የሚባለው የፍራንክ ችሎት መንግስት ቅጣት እንዲከፍሉ ክስ ያቀረበባቸውን ሰዎች ህይወታቸውን እና ገቢያቸውን በመመርመር በነጻ የሚሰናቱበት ነው፡፡
አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ጥፋተኛ እና ያልተገባ ባህሪ ያለው ሰው ሲያጋጥማቸው ከአባታዊ ቁጣ ጋር ጭምር ፍርድ ይሰጣሉ፡፡
ዳኛው በመጨረሻ የስራ ዘመናቸው ወቅት የነበሯቸው ችሎቶች በቴሌቪዥን ፕሮግራም መልክ ተቀርጸው ለተመልካቾች ቀርበዋል፡፡
3.2 ሚሊዮን ተመልካች ያለው የዳኛ ፍራንክ የኢንስታግራም ገጽ፣ ከፓንክሪያቲክ ካንሰር ጋር ሲፋለሙ የቆዩት ፍራንክ በ88 አመታቸው ህይወታቸው አልፏል የሚል መልዕክትን ትላንትና ምሽት ላይ አስነብቧል፡፡
የአሜሪካው ሮድ አይላንድ ግዛት አስተዳዳሪ ዳን ማኪ፣ “ፍራንክ ካፓሪዮ የደግነት እና ርህራሄ ምልክት ነበሩ፤ ፍትህ ከሰብአዊነት ጋር የተዋሀደ እንደሆነም አስተምረውናል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በዳዊት በሪሁን