የእስራኤል ጦር የጋዛ ከተማን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር ከ60 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ተጠባባቂ ጦር አባላት ጥሪ አስተላልፏል፡፡
የሀገሪቱ ጦር ቃል አቀባይ ሰራዊቱ በአሁኑ ወቅት በጋዛ ከተማ ድንበር አቅራቢያ ሰፍሮ እንደሚገኝ ይፋ አድርጓል፡፡
የእስራኤል መንግስት የጋዛ ሰርጥ ግዙፉ የከተማ ማዕከል እንደሆነ የሚነገርለትን የጋዛ ከተማን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር ወስኗል፡፡
በአሁኑ ወቅት ዘይቶን እና ጃባሊያ በተባሉ የጋዛ ከተማ አጎራባቾች በሰፊው እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው የሀገሪቱ ጦር ከተማውን ለመቆጣጠር በሚደረገው ዘመቻ ውስጥ ተሳታፊ እንደሚሆን ተነግሯል፡፡
የቤንያሚን ኔታንያሁ አስተዳደር የጦር ካቢኔ ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚያደርስበትን ትችት ወደ ጎን በማለት የጋዛ ከተማን ሙሉ ደህንነት ለመቆጣጠር ወስኗል፡፡
በተጨማሪም የሀማስ ታጣቂዎች ጠንካራ ይዞታ እንደሆነ የሚነገርለትን ይህን ከተማ ጦሩ በፍጥነት በቁጥጥሩ ስር እንዲያደርግ ካቢኔው ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
የእስራኤል መንግስት በከተማዋ ሙሉ ዘመቻ ከመጀመሩ በፊት፣ ንጹሀን አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ እንደሚሰጥ ቃል ገብቷል፡፡
ሆኖም የቴልአቪቭ አጋር የሆኑ ብሪታንያን የመሳሰሉ ሀገራት ዘመቻው ተጨማሪ የንጹሀን ሞት እና መፈናቀልን የሚያስከትል ነው በሚል ተቃዎሟቸውን እያሰሙ ነው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከሰሞኑ ሀማስ ባቀረበው የ60 ቀናት የተኩስ አቁም ጥያቄ ዙሪያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በነገው ዕለት ምላሽ ይሰጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ስካይ ኒውስ ዘግቧል፡፡
በተኩስ አቁሙ 10 በህይወት የሚገኙ እና 18 ህይወታቸው ያለፈ ታጋቾችን ለመልቀቅ፣ በምትኩ 200 የሚጠጉ ሴቶች እና ህጻናት ፍልስጤማውያን እስረኞች ከእስራኤል እስር ቤቶች እንዲለቀቁ ሀማስ ጥያቄ አቅርቧል፡፡
እንደ እስራኤል የደህንነት መረጃ ከሆነ፣ በአሁኑ ወቅት በሃማስ ታጣቂዎች እጅ ላይ 50 ታጋቾች የሚገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል 20 የሚሆኑት በህይወት ያሉ መሆናቸውን መረጃው ያመላክታል፡፡
በዳዊት በሪሁን