በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወነው ስኬታማው የኮሪደር ልማት ሥራ የስፖርት ማዘውተሪያዎችን በስፋት ያካተተ በመሆኑ የኢትዮጵያን ስፖርት ለማሳደግ ትልቅ አስተዋፅዖ እንደሚያበረክት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፣ የአዲስ አበባ ከተማን ሁለንተናዊ ገፅታ ከመቀየር አንፃር ከፍተኛ አስተዋፅዖ በማበርከት ላይ የሚገኘው የኮሪደር ልማት፣ በአሁኑ ወቅት ለውጥ እና ዕድገት መምጣቱን አፍ አውጥቶ መናገር ጀምሯል ብለዋል፡፡
ከኮሪደር ልማቱ ጋር ተያይዞ የስፖርት ማዘውተሪያዎችን ለመገንባት መንግስት ትኩረት ከመስጠትም በላይ ትልቅ መዋለ ንዋይ ያፈሰሰበት መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከአፍሪካ የእግር ኳስ መድረክ መራቁ የስፖርቱን ቤተሰብ የሚያስቆጭ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፣ አሁን በአዲስ አበባ ከተማ በተገነቡ ከ100 በላይ በሚሆኑ የስፖርት ሜዳዎች ላይ ታዳጊዎች ከአልባሌ ውሎ ታቅበው ስፖርታዊ እንቅስቃሴ የሚያደርጉበት ሁኔታ መፈጠሩን ገልፀዋል፡፡
ይህ ልምምድ እያደገ ሲሄድ በየሰፈሩ ጥራታቸውን ጠብቀው የተሠሩ የስፖርት ማዘውተሪዎች፣ ሀገራቸውን የሚያስጠሩ ስፖርተኞችን የማፍራታቸው ጉዳይ የማያጠራጠር ይሆናልም ነው ያሉት፡፡
ፌዴሬሽኑን በመውቀስ ሳይሆን በመሥራት እና በዘርፉ ላይ ኢንቨሰት በማድረግ ነው ለውጥ ማምጣት የሚቻለውም ብለዋል፡፡
በዘርፉ ላይ በሚገባ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ ከተሠራ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ አፍሪካ ዋንጫ የማይመለስበት ምክንያት እንደማይኖር ተናግረዋል፡፡
በማሬ ቃጦ