ከአየር ንብረት ለውጥ ቀውስ ወደ አረንጓዴ እድል

You are currently viewing ከአየር ንብረት ለውጥ ቀውስ ወደ አረንጓዴ እድል

ዓለም እየተባበሰ ከመጣው የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስ ጋር ትግል እያደረገ ባለበት በዚህ ወቅት አፍሪካ ለዓለም ከችግሩ የመውጫ መንገድ የሆነ መፍትሄ ይዛ መጥታለች።

በአረንጓዴ የማይበገር ኢኮኖሚ አማካኝነት። ይህ ትልቅ ራዕይ በአዲስ አበባ ከጳጉሜን 3 እስከ 5 ቀን 2017 ዓ.ም በሚካሄደው ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ዋነኛ የትኩረት ማዕከል ከሆኑ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው።

በጉባኤው የሚሳተፉ የሀገራት መሪዎች፣ ተመራማሪዎች፣ ኢኖቬተሮች፣ የግሉ ዘርፍ እና የተለያዩ ማህበረሰቦች የአየር ንብረት ለውጥ አደጋዎችን ወደ ዘላቂ እድገት መቀየር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ይመክራሉ።

በአህጉሪቱ የአረንጓዴ እና አይገበሬ ኢኮኖሚ መጻኢ ጊዜ የሚቀይሱ የመፍትሄ ሀሳቦች ይቀርባሉ።

ጉባኤውን የምታስተናግደው ኢትዮጵያ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት ስትራቴጂ ቀርጻ እየሰራች ትገኛለች።
ስትራቴጂው ግብርና፣ ደን ልማት፣ ኢነርጂ እና ትራንስፖርትን ጨምሮ የተለያዩ ዘርፎችን አቅፎ የያዘ ነው።

የአረንጓዴ አሻራ የታዳሽ ኃይል ምንጮችን ከማስፋት ስራ ጋር ተዳምሮ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ማጣጣሚያ እቅድ ትግበራን፣ አይበገሬነት መገንባትና ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገትን የማረጋገጥ ሚዛን አስጠብቃ እየተጓዘች ትገኛለች።

ጉባኤው በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ላይ ለመምከር ከመሰባበብ ባሻገር በአፍሪካ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት ለተጀመረው ጉዞ እንደ አቀጣጣይ ሞተር ሆኖ የሚያገለግል ነው።

ይህ የኢኮኖሚ አማራጭ ዘላቂ እድገትን ከማህበረሰቦች የአደጋ መቋቋሚያ አቅም መገንባት እና የተፈጥሮ ስርዓትን መጠበቅ ጋር የተቆራኘ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
በጉባኤው ከአፍሪካ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ አጀንዳ ጋር የተገናኙ አጀንዳዎች እንደሚቀርቡም ተመላክቷል።
በተፈጥሮ እና ቴክኖሎጂ ተኮር መፍትሄዎች አማካኝነት የካርቦን ልህቀትን መቀነስ፣ አረንጓዴ መሰረተ ልማት ግንባታን ማጠናከር እና ዘላቂ ልማት መፍጠር ላይ ውይይቶች ይደረጋሉ።


የአየር ንብረት መላመድ ስትራቴጂዎች በመፍጠር እና የማይበገር አቅም በመገንባት ማዕቀፍ ውስጥ ለአደጋዎች ማህበረሰብ ተኮር ምላሽን ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የሀገራት ተሞክሮ ይቀርባል።
አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ስራዎች ከውጭ ሀገራት እና አጋሮች ድጋፍ ከመጠበቅ ይልቅ አካባቢ ተኮር የሆኑ አረንጓዴ ፋይናንስን ጨምሮ የተለያዩ የገንዘብ አማራጮች እና መፍትሄዎችን መፈለግ በጉባኤው አጽንኦት የሚሰጠው ጉዳይ ነው።
ወጣቶችና ሴቶች በጉባኤው ላይ ይበጃሉ የሚሏቸውን የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሄዎች ያቀርባሉ።
የአዲስ አበባው ጉባኤ የአየር ንብረት ለውጥ አደጋን ወደ አረንጓዴ እድልና አይበገሬነት የመቀየር ጉዞ የሚያጸና ማዕቀፍ ይሆናል ተብሎም ይጠበቃል።
ጉባኤው ስኬታማ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ እየገነባች የምትገኘው ኢትዮጵያ በጉዳዩ ላይ ተከታይ ሳትሆን የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች መሆኑን የምታሳይበት ነው።
ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ህብረት በጋራ የሚያዘጋጁት ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ “ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መፍትሄዎችን ማፋጠን፥ የአፍሪካን አረንጓዴ ልማት በፋይናንስ መደገፍ” በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄድ ሲሆን መሪ ጭብጡ ከአረንጓዴ ልማት እና ኢኮኖሚ የተቆራኘ ነው።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review