የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች ለዝውውር ያወጡት ወጪ ከምንግዜውም በላይ ከፍተኛ ሆኗል፡፡ የዝውውር መስኮቱ ሊዘጋ ገና 10 ቀናት እየቀሩ ክለቦቹ 2.37 ቢሊየን ዶላር ወጪ አድርገዋል፡፡
በዝውውር መስኮቱ ክለቦች በስድስት አጋጣሚ ከዚህ ቀደም ለአንድ ተጫዋች ያወጡትን ከፍተኛ ገንዘብ አሻሽለው ተጫዋቾችን አስፈርመዋል፡፡
ብሬንትፎርድ ፣ ቦርንማውዝ ፣ በርንሌይ ፣ ኖቲንግሃም ፎረስት(ሁለት ጊዜ) እና ሊቨርፑል ክብረወሰን አሻሽለው ረብጣ ዶላራቸውን ተጫዋቾች ላይ ፈሰስ ያደረጉ ክለቦች ናቸው፡፡
ቢቢሲ ስፖርት ትራንስፈር ማርኬትን ጠቅሶ እንደዘገበው የእስካሁኑ ውዱ ፈራሚ ፍሎሪያን ቨርትዝ ነው፡፡ ተጫዋቹ ከ ባየር ሊቨርኩሰን ሊቨርፑልን ሲቀላቀል እስከ 116 ሚሊየን ፓውንድ ወጪ እንደሚሆንበት ተነግሯል፡፡
አጠቃላ የዝውውር ገንዘቡ ከ2.37 ቢሊየን ፓውንድ ከፍ የሚልበት እድል የሰፋ ነው፡፡ አርሰናል ኤቤሬቺ ኤዜን ለማስፈረም ጫፍ ደርሷል፡፡ ቶተንሃም ቢያንስ ሁለት ተጫዋቾችን ማስፈረሙ የማይቀር ነው፡፡
ሊቨርፑል ምናልባትም ሌላ ክብረወሰን አሻሽሎ አሌክሳንደር ኢዛክን ሊያስፈርም እንደሚችል እየተጠቆመ ይገኛል፡፡ ቼልሲ ፣ ማንችስተር ዩናይትድ እና ኒውካስትል ዩናይትድ ተጫዋቹ ሳያስፈርሙ የዝውውር መስኮቱ ይዘጋባቸዋል ተብሎ አይጠበቅም ፡፡
በሸዋንግዛው ግርማ