የአዲስ አበባ ከተማን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መሰራቱ የፀረ ሰላም ሃይሎችን እቅድ ማክሸፍ ማስቻሉ ተገለፀ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ የ2018 ዓ.ም የቅንጅታዊ ስራዎች እቅድ ትውውቅና ከባለድርሻ አካላት ጋር የትስስር ስራዎች የፊርማ ስነ-ስርዓት አካሂዷል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ፤ ከተማዋ እንደመዲናነቷ የነዋሪዎቿን ሰላምና ደህንነት ከማስጠበቅ ባለፈም በርካታ ሀገርአቀፍ እና አለምአቀፍ ኩነቶችን የምታካሂድ በመሆኗ ሰላሟን ማስጠበቅ በልዩ ትኩረት ሲከናወን ቆይቷል ብለዋል፡፡

በዚህም መዲናዋ ስኬታማ ጉባኤዎችን ማስተናገዷን የገለፁት ሃላፊዋ፤ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መሰራቱ የፀረ ሰላም ሃይሎችን እቅድ ማክሸፍ ማስቻሉን ገልፃዋል፡፡
በ2018 ዓ.ም የምታከናውናቸው የሰላምና ደህንነት ተግባራት ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑም፤ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ከቅድመ ዝግጅት አንስቶ ያሉ ህዝቡን ማዕከል ያደረጉ ሰላምና ደህንነትን የማስከበር ስራዎችን በቅንጅት ከባለድርሻ አካላት ጋር ማከናወን ይጠይቃታል ሲሉ ኃላፊዋ ተናግረዋል፡፡
በ2017 በጀት ዓመት በከተማዋ የሰላምና ፀጥታ ተግባራትን በማከናወን የታዩ አመርቂ ውጤቶች ተጠናክረው ይቀጥሉ ዘንድ የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ የ2018ዓ.ም የቅንጅታዊ ስራዎች እቅድ ትውውቅና ከባለድርሻ አካላት ጋር የትስስር ስራዎች የፊርማ ስነ ስርዓት አካሂዷል፡፡
በመድረኩም የተገኙ ባለድርሻ አካላት ከዚህ ቀደም የተገኙ ድሎችን ለማስጠበቅ እና የነዋሪውን ጥያቆዎች ለመመለስ ቅንጅታዊ ስራዎችን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡
በታምሩ ደምሴ