በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 15 ሺህ 612 ቶን የቅመማቅመም ምርት ለውጪ ገበያ በማቅረብ 14 ነጥብ 94 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ማግኘት ተችሏል።
የቅመማቅመም ምርቱ የተላከው ወደ ሕንድ፣ ግብጽ፣ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች፣ የመን፣ ኬንያ፣ ኢራቅ እና ፓኪስታን መሆኑን በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የቅመማቅመም ልማት ዴስክ ኃላፊ ሞገስ አሸናፊ ተናግረዋል።
እንደ ሀገር ፋይዳ ያላቸውን የቅመማቅመም ዓይነቶች የመለየትና የተለያዩ መረጃዎችን ከየክልሎች የመሰብሰብና የማደራጀት ሥራ መከናወኑንም ለኢዜአ ገልጸዋል።
በዚህም ከደጋ ቅመማቅመም፤ ጥቁር አዝሙድ፣ ነጭ አዝሙድ፣ ድንብላል፣ አብሽ፤ ከራይዞም ሰብሎች፤ ዝንጅብል፣ ዕርድ፣ በርበሬ፣ ኮረሪማ፣ ቁንዶበርበሬ፣ ሄል፤ ከመድኃኒታማና መዓዛማ ሰብሎች ሮዝመሪ፣ ጤናዳም፣ በሶብላ፣ ሎሚሳር፣ ከርከዴ ተለይተው ድጋፍና ክትትል እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ከቅመማቅመም ጥራትና ግብይት ሂደት ጋር ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የቅመማቅመም የጥራትና ግብይት መመሪያ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ መገባቱን አስታውቀዋል።
መመሪያውን ወደ አዋጅ ለማሳደግ ረቂቁ ተጠናቅቆ ለግብርና ሚኒስቴር መላኩንም ጠቁመዋል።
በ2017 በቅመማቅመም ሰብል ከተሸፈነው 683 ሺህ 294 ሔክታር 1 ሚሊየን 210 ሺህ 600 ቶን ምርት መሰብሰቡን ተናግረዋል።
በተያዘው የበጀት ዓመትም 17 ሺህ 194 ቶን የቅመማቅም ምርት ለውጪ ገበያ በማቅረብ 16 ነጥብ 176 ሚሊየን ዶላር ለማግኘት መታቀዱን ማመላከታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 2 ሚሊየን 268 ሺህ 984 ወገኖች በቅመማቅመም ልማት መሰማራታቸውንም አስረድተዋል።