እስራኤል ሁሉንም ታጋቾቿን ለማስለቀቅ ንግግር ልትጀምር መሆኑን ገለጸች

You are currently viewing እስራኤል ሁሉንም ታጋቾቿን ለማስለቀቅ ንግግር ልትጀምር መሆኑን ገለጸች

AMN- ነሐሴ 16/2017 ዓ.ም

ካቢኔያቸው የእስራኤል መከላከያ ጋዛን ለመቆጣጠር ያወጣውን ዕቅድ ለማፅደቅ መወሰኑን ተከትሎ ታጋቾችን ለመማስለቀቅ የሚያስችል ንግግር ለማድረግ መዘጋጀታቸውን የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ገልጸዋል፡፡

ባሳለፍነው ሰኞ በግብፅ እና ኳታር አሸማጋይነት የቀረበውን የ60 ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነት ሃማስ የተቀበለው ቢሆንም፣ በእስራኤል በኩል ከስምምነት አልተደረሰም፡፡

የእስራኤል መከላከያ ጋዛን ለመቆጣጠር እና ሃማስን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማሸነፍ ያወጣውን ዕቅድ እንደሚያፀድቅም አስታውቀዋል፡፡

ኔታንያሁ በቀጣይ ስለሚኖረው ንግግር የሰጡት ማብራሪያ በሌለበት ሁኔታ፣ ሃማስን ማሸነፍ እና ታጋቾቻችንን ከማስለቀቅ ጎን ለጎን የሚከናወኑ ተግባራት ናቸው ብለዋል፡፡

በግብፅና ኳታር አሸማጋይነት የቀረበውን የ60 ቀናት የተኩስ አቁም ዕቅድ የእስራኤል ባለሥልጣናት አለመቀበላቸውን ተከትሎ ሃማስ የኔታንያሁን አካሄድ ወቅሷል፡፡

እስራኤል በተኩስ አቁም ዕቅድ ላይ ልትስማማ የምትችለው ሁሉም የእስራኤል ታጋቾች በአንድ ጊዜ እንደሚለቀቁ በዕቅዱ ከተካተተ ብቻ መሆኑን አስታውቃለች፡፡

ጦርነቱ እንዲያበቃም ሃማስ ትጥቅ ሊፈታ፣ ጋዛም በእስራኤል ቁጥጥር ሥር እንድትሆን እና ከሃማስ እና ፍልስጤም ውጭ በሆነ አካል እንድትተዳደር ማድረግ የግድ መሆኑን እስራኤል ታምናለች፡፡

እንደ ቢቢሲ ዘገባ በትላንትናው እለት በጋዛ ምስራቃዊ ክፍል ከፍተኛ ጥቃት የደረሰ ሲሆን፣ ሀኪሞች እና ዓለም አቀፍ ተቋማት አንድ ሚሊየን የጋዛ ነዋሪዎችን ወደ ደቡባዊ ክፍል ለማዛወር ለተያዘው እቅድ ዝግጁ እንዲሆኑ እስራኤል አስጠንቅቃለች፡፡

የረድኤት ድርጅቶች እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በበኩላቸው፣ ከአካባቢው መዛወር የሚፈልጉትንም ሆነ በሥፍራቸው መቆየት የወሰኑ ዜጎችን ከመርዳት እንደማይቦዝኑ ገልፀዋል፡፡

በማሬ ቃጦ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review