የኮሪደር ልማት በርካታ ትችቶችን አልፎ እምርታ ማሳየቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ

You are currently viewing የኮሪደር ልማት በርካታ ትችቶችን አልፎ እምርታ ማሳየቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ

AMN- ነሐሴ 16/2017 ዓ.ም

የኮሪደር ልማት ገና በአዲስ አበባ ከተማ ሲጀመር፣ በርካታ ትችቶች እና ነቀፌታዎች ሲሰነዘሩበት እንደነበርና ያንን ሁሉ አልፎ ትልቅ እምርታ ማስመዝገቡን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመደመር ሀሳብ ላይ የጻፉት አራተኛውንና “የመደመር መንግሥት” የተሰኘውን አዲስ መጽሐፍ በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ ከኮሪደር ልማቱ ጋር በተያያዘ የተገኘውን ስኬት አንስተዋል።

የመዲናዋን ገፅታ በብዙ መልኩ እየቀየረ የሚገኝው የኮሪደር ልማት፣ ከመዲናዋ አልፎ በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ጭምር እየተተገበረ እና ትልቅ ለውጥ እያመጣ እንደሚገኝ አመላክተዋል፡፡

የኮሪደር ልማት ሥራው ከኢትዮጵያ ባለፈ ለአፍሪካ ከተሞችም ተምሳሌት እየሆነና ልምድ እየተቀሰመበት እንደሚገኝም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ የኮሪደር ልማት ሥራ አርቆ በማሰብ እና አልቆ በመስራት የመጣ ሀገርን የሚያኮራ ተግባር የተሰራበት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

ብዙዎች በሩቅ በሌሎች ሀገራት እያዩት ሲመኙት የነበረው ልማት፣ በሀገር ውስጥ እውን መሆኑ፣ ዜጎች በሀገራቸው ለመኖር፣ ለመሥራት እና በሀገራቸው እንዲኮሩ ከማድረጉም ባሻገር፣ የሌላ ሀገር ዜጎች ኢትዮጵያን ለመጎብኘት እንዲነሳሱ ያደረገ ልማት መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review