የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የተገነቡ የተሽከርካሪ ማቆሚያዎች እና የገበያ ማዕከላትን መርቀው ስራ አስጀመሩ

You are currently viewing የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የተገነቡ የተሽከርካሪ ማቆሚያዎች እና የገበያ ማዕከላትን መርቀው ስራ አስጀመሩ

AMN- ነሐሴ 16/2017 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የተገነቡ የተሽከርካሪ ማቆሚያዎች እና የገበያ ማዕከላትን እንዲሁም የታክሲና የአውቶብስ መጫኛ እና ማውረጃዎችን መርቀው ስራ አስጀምረዋል።

ከሜክሲኮ እስከ ለገሀር ባለው አካባቢ ብቻ 2 ሺህ 145 ተሽከርካሪዎችን በአንድ ግዜ ማቆም የሚችሉ 13 የተሽከርካሪ ማቆሚያዎች እና 1 ሺህ 624 ታክሲና አውቶብስ በአንድ ግዜ ማስተናገድ የሚችሉ መጫኛ እና ማውረጃዎች ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት መደረጋቸውን ከንቲባ አዳነች ተናግረዋል።

በዚህ ክረምት ወደ 19 ሺህ የሚጠጉ ፕሮጀክቶች ተገንብተው ወደ አገልግሎት እየገቡ መሆናቸውን ከንቲባዋ ተናግረዋል፡፡

ዛሬ የተመረቁት ፕሮጀክቶች በከተማዋ የመንገድ ትራፊክ መጨናነቅ በነበረባቸው እና የቆሸሹ እና የተጎሳቆሉ የነበሩ ቦታዎችን በማጽዳት እና የትራፊክ እንቅስቃሴውን ማሳለጥ የሚያስችሉ እና የስራ እድልን ጭምር የሚፈጥሩ ፕሮጀክቶች መገንባታቸውን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።

የተሽከርካሪ ማቆሚያዎቹና የታክሲና የአውቶብስ መጫኛ እና ማውረጃዎቹ 300 የሚደርሱ ሱቆች፣ 50 መጋዘኖች፣ 80 የሚደርሱ መጸዳጃ ቤቶች ፣ የደህንነት ካሜራዎች፣ ከአንድ ማዕከል ቁጥጥር ለማድረግ የሚያስችሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የተሟሉላቸው ዘመናዊ ፕሮጀክቶች መሆናቸው ተገልጿል።

ከተመረቁት ፕሮጀክቶች መካከል ባሻ ወልዴ ችሎት አካባቢ የሚገኘው ስኬት የገበያ ማዕከል፣የተሽከርካሪ ማቆሚያ እና ፕላዛ፣ የአፍሪካ ህብረት የገበያ ማዕከልና የተሽከርካሪ ማቆሚያ፣ በሜክሲኮ አካባቢ የተገነቡ የተሽከርካሪ ማቆሚያዎችና የታክሲና አውቶብስ ተርሚናሎች ይገኙበታል።

በሰብስቤ ባዩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review