በተጠናቀቀዉ የበጀት አመት ከ300 ሺህ በላይ ቤቶች በተለያዩ አማራጮች ተገንብተዉ ለዜጎች ተደራሽ ሆነዋል

You are currently viewing በተጠናቀቀዉ የበጀት አመት ከ300 ሺህ በላይ ቤቶች በተለያዩ አማራጮች ተገንብተዉ ለዜጎች ተደራሽ ሆነዋል

AMN ነሃሴ 16/2017

ለዜጎች የመኖሪያ ቤት የፍላጎት ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ስኬታማ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒሰትር ዴኤታ ሔለን ደበበ ገለጹ፡፡

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒሰትር ዴኤታ ሔለን ደበበ እንደገለጹት የዜጎችን ፈጣን የክትመት ምጣኔ መጨመርን ተከትሎ የመኖሪያ ቤት ፍላጎት በየወቅቱ እያደገ መጥቷል።

ቀደም ሲል የቤት አቅርቦት በመንግስት ብቻ ይሸፈን እንደነበር አስታውሰው ይህ አሰራር ካለው ፍላጎት ጋር የሚጣጣም ባለመሆኑ የዜጎችን የቤት ጥያቄ ለመመለስ አዳጋች አድርጎት መቆየቱን ጠቅሰዋል።

የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ተደራሽነት ላይ ለውጥ ማምጣተ እንዲቻል መንግስት የተለያዩ የቤት ልማት ፕሮግራሞችን ነድፎ ተግባራዊ ማድረግ ጀምሯል ብለዋል።

ለዚህም የህግ ማዕቀፍን ማሻሻል፣ የግል አልሚዎች በስፋት የሚሳተፉበትን እድል ማመቻቸት ተጠቃሽ ስለመሆናቸው አንስተዋል።

በአስር አመት መሪ የልማት እቅድ 4 ነጥብ 4 ሚሊዬን ቤቶችን በተለያዩ አማራጮች ለዜጎች ለማቅረብ መታቀዱን ጠቁመው፤ ከዚህ ውስጥ በየዓመቱ 440 ሺህ ቤቶች ተደራሽ ማድረግ ይጠበቃል።

ይህ እቅድ በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የዜጎች የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ መሆኑንም አንስተዋል።

በዚህም ባለፉት የለውጥ አመታት እቅዱን ለማሳካት በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤት መመዝገቡን ገልጸው፤ በ2017 በጀት አመት ከ300 ሺህ በላይ ቤቶችን በተለያዩ አማራጮች ለዜጎች ተደራሽ ማድረግ መቻሉን አስታውቀዋል።

በመንግስትና በግል አጋርነት የሚገነቡ መኖሪያ ቤቶችን በስፋት የማልማት ስራም አንዱ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅት የ70/30 የቤት ልማት ፕሮግራም በአዲስ አበባ በስፋት እየተተገበረ ሲሆን ከ89 ሺህ በላይ ቤቶችን ለመገንባት በተገባው ውል ግንባታ እየተከናወነ ይገኛል።

ይህ ጅማሮ እንደ ሀገር የቤት አቅርቦት አማራጭን ለማስፋት ጥሩ መነቃቃትን የፈጠረና የግሉ ዘርፍ በመሰረተ ልማት አቀርቦት ዙሪያ የነበረበትን ጫና ያቃለለ ነው ብለዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተጀመረው የክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ባህል እየሆነ መምጣቱን ጠቁመው፤ የተሟላ መሰረተ ልማት ያሟሉ ቤቶች ለዜጎች ተደራሽ እንዲሆኑ እድል መፍጠሩን ገልጸዋል።

በዚህም ከመኖሪያ ቤት አቅርቦት በዘለለ የዜጎችን ኑሮ በዘላቂነት የሚያሻሽል የቤት አቅርቦት ተግባራዊ በማድረግ ምሳሌ የሚሆን ስራ ተከናውኗል ነው ያሉት።

እንዲሁም የተቀናጀ የኮሪደር ልማት ከመንገድ መሰረተ ልማት በተጨማሪ ለቤት አቅርቦት ተጨማሪ አቅም መፍጠር ችሏል ሲሉ ሚኒስትር ደኤታዋ መናገራቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በዚህ ሒደት አዲስ አበባን ጨምሮ በሁሉም ክልሎች በሚባል ደረጃ በአስቸጋሪ የቤትና የኑሮ ሁኔታ ውስጥ ለነበሩ ዜጎች እፎይታን መስጠት የቻለ የልማት ስራ መከናወኑን ገልጸዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review