ለአለም ስጋት የሆነው የአየር ንብረት ለውጥ እንደ ኢትዮጰያ ላሉ በማደግ ላይ ለሚገኙ አገራት የችግሩ ሰለባ ሲሆኑ ይስተዋላል። ይህንን ችግር ለመቀልበስ ኢትዮጵያም ከስድስት አመት በፊት የአረንጓዴ አሻራ ልማት በአገር አቀፍ መተግበሯ ምክንያት መሆኑ ይጠቀሳል ። አዲስ አበባ ከተማ የችግሩ ገፈት ቀማሽ ላለመሆን የበኩሏዋን ሀላፊነት እየተወጣች የምትገኝ ከተማ ናት ። የአረንጓዴ መሰረተ ልማትን ትግበራ የስማርት ሲቲ አንዱ አካል አድርጋ ስራዎችን እያከናወነች ትገኛለች።
የከተሞች ልማት መስፈርቶች ውስጥ የአረንጓዴ ሽፋን ዋነኛው በመሆኑ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንዲሉ ለውበትም ለተፈጥሮም ተገቢውን ዲፕሎማሲያዊ ምላሽ እየሰጠች ትገኛለች ። የከተማ እድገት በህንፃዎች ማማር ብቻ እይገለፅም ። ከተፈጥሮ ጋር የሚኖራቸው ሰላማዊ መስተጋብርም ከተማ ያስብላል ። ንፁህ አየር ለመማግ በቂ የዝናብ መጠን ለማግኘት ተፈጥሮ ጋር ጥሩ ዲፕሎማሲ ማዳበር እንደሚገባ ይታመናል ። የአየር ንብረት ማለት በአንድ ሥፍራ ያለው የአየር ፀባይ በጊዜ ሒደት የሚያሳየው አማካይ ውጤት ነው መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ከተማዋ ያላትን የተፈጥሮ ሃብት የመነከባከብ ስራዎችን በስፋት እያከናወነች ትገኛለች ለዚህ ማሳያ ወንዞችን ማንሳት ይቻላል ። በመዲናዋ የሚገኙ እነዚህ ወንዞች የመጥፎ ጠረን እና የብክለት መገለጫ ሆነው ከከተሜነት ፅንስ ሃሳብ ጋር ሆድና ጀርባ ሆነው ዓመታተን ቢያሳልፉም አሁን ላይ የመዝናኛ የውበት መገለጫ እንዲሆን እየተበጁ ይገዓሉ ፡፡ በተጨማሪም በሁለት ዓመታት በተሰሩ የኮሪደር ልማት አማካኝነት የከተማዋ የአረንጓዴ ልማት ስራዎች የከተማዋን ገፅታ በመቀየር ውብ እና ተወዳዳሪ ከተማ እንድትሆን አድርጓታል።
ከተማዋን እንደ ስሟ ውብ ከማድረግ አኳያ በርካታ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። በተሰሩ ስራዎችም የዜጎችን ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ ለማድረግ ተችሏል። አንድን ከተማ ስማርት ናት ለማለት መመዘኛዎች ሲኖሩት ከዚያ ውስጥ አንዱ የአረንጓዴ ሽፋኗን ቢያንስ 30 በመቶ መሆን ይጠበቅበታል። አዲስ አበባ ከተማ ከአመታት በፊት አጠቃላይ የአረንጓዴ ሽፋኗ 2.8 በመቶ ብቻ እንደነበር ይታወሳል።
ከ2010 ዓ.ም ወዲህ በተለይም በሁለት እና ሶስት ዓመታት ግዜ ውስጥ አጠቃላይ የአረንጓዴ ሽፋኗን ከማሳደግ አኳያ ከ22 በመቶ በላይ ማድረሷን የአዲስ አበባ ከተማ አከባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ አሰግደው ሀይለጊዎርጊስ ለኤ ኤም ኤን ዲጅታል ተናግረዋል።
በዚህ ጉዳይ የከተማ አስተዳደሩ ከተማዋ ስማርት ምቹ እና ፅዱ እንድትሆን እየተሰራ ባለው የአረንዴ አሻራ ልማት በቅንጅት፣ በትብብር በመሰራቱ ትልቅ ውጤት መምጣቱን ይገልፃሉ። በአገር ደረጃ የተጀመረው የአረንጓዴ ልማት ንቅናቄ ለመዲናዋ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ እና ለአለም ትልቅ ተሞክሮ መሆኑን ያስረዳሉ ። የኮሪደር ልማት በከተማዋ በስፋት የተሰራበትን ሁኔታ አንስተው፣ የወንዞች እና የወንዞች ዳርቻ ልማት 45 ኪሎ ሜትር በላይ ሽፋን ያገኘ ፕሮጀክት መሆኑን ይገልጻሉ።
የተሰሩት ስራዎች የገፅታ ስታንዳርድ በጠበቀ መንገድ ከአረንጓዴ ልማት ጋር እየተሳሰረ የተሰራ ነው በማለት ገልፀዋል ። ከተማዋን አረንጓዴ ለማድረግ በተለይም የአገር በቀል ችግኞችን እና ፍራፍሬ ተክሎችን ለመትከል ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል ። በወንዞች ላይ እየተሰራ ባለው ስራ አገር በቀል ችግኞችን በመትከል ስነ-ምህዳሩ እንዲታከም መደረጉን ተናግረዋል ። ከዚህ በፊት የነበሩ መናፈሻ ቦታዎች በአግባቡ እንዲታደሱ እና ጥቅም ላይ እንዲውሉ መደረጋቸውን አስረድተዋል።
በተቋም ደረጃ ችግኞችን በመትከል እና የተተከሉትን በመንከባከብ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ምክትል ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል። ከወንዞች እና የወንዞች ልማት ዳርቻ ልማት ፕሮጅክት ከአከባቢ ጥበቃ አኳያ ፋይዳው ክፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል። ከእንጦጦ እስክ ፒኮክ ድረስ በወንዞች እና የወንዞች ዳርቻ ላይ የሚሰሩ ስራዎች ከባቢያዊ አየርን ከመጠበቅ አኳያ ሚናው ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል። እንዲሁም ከቀበና በግንፍሌ አድርጎ ፒኮክ የሚወስደውን የወንዞች ዳርቻ ስታንዳርዱን የጠበቁ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝም ነው የገለፁት፡፡
ለእነዚህ በታዎች ገባር የሆኑ ትናንሽ ወንዞችን እንዲታከሙ እና ገፅታቸውን እየተቀየረ መሆኑን ገለፀዋል ። ይህ በመሆኑ ከዚህ ቀደም የነበረውን የወንዞችን ታሪክ መቀየሩን ገልፀው፣ ቆሻሻ መጣያ፣ የፍሳሽ ማስወገጃ ስለነበሩ ከብክለት ጋር ከፍተኛ ችግሮች ውስጥ የዘለቁ እንደነበሩ አስታውሰዋል። መዲናዋ ከዚህ ቀደም ወንዞች እና በወንዞች ዳርቻዎችን አፈር መሸረሸር ፣ ውሀ ከመበከሉ በተጨማሪ ክረምት በመጣ ቁጥር የወንዞችን ዳር ይዘው የሚኖሩ ዜጎች ህይወት እና የንብረት ለጎርፍ የተጋለጡ እንደነበሩ አስታውሰዋል።
ይህም ስነ-ምህዳሩ በአግባቡ ባለመጠበቁ የብዝሀ ህይወት ጉዳይ አደጋ ተጋርጦበት እንደነበር እንደነበሩ ያስታውሳሉ ። ከዚህ ቀደም በመዲናይቱ የሚገኙ ወንዞች ለወጣቶች እና ለህፃናት መዝናኛነት እየዋሉ አልነበረም ያሉት አቶ አሰግደው ፣ የስራ ዕድል ፈጠራ ምንጭ እንዳልነበሩ ፣ የከተማዋን ገፅታ ከማበላሸት በዘለለ ፋይዳ እንዳልነበራቸው ገልፀዋል።
ወንዞቹ በከተማዋ ነዋሪዎች ላይ የሚያደርሱት አሉታዊ ተፅእኖ ከፍተኛ እንደነበር እና ችግሩን በጥልቀት በመረዳት በዘላቂነት ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ነው የተናገሩት ፡፡ ወንዞችን በማልማት ብክለትን ከመከላከል አኳያ ፕሮጀክቱ በህግ እየተመራ እንደሚገኝ ተናግረዋል። በወንዞች ላይ በስፋት እየተሰራ ያለው ስራ የወንዞች የብክለት ታሪክ እዲቀንስ ብቻ ሳይሆን እንዲያከትም በትብብር እየተሰራ ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል።
በተለይም አሁን በወንዞች ዳርቻ ልማት የደረሰባቸው ቦታዎች በልማቱ ምክንያት ብክለቶቹ መቀነሳቸው አስረድተዋል ። እንደ ምክትል ስራ አስኪያጁ ገለፃ ፣ብክለት ሲቆም የተስተካከለ አየር ሲኖር ለሰው ልጅ ህይወት ለእፅዋት፣ ለሁሉም ጤናማነት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ሲሉ ተናግረዋል።
ሁለተኛነት ያስቀመጡን የተስተካከለ ስነ-ምህዳር እንዲኖር ከምንም በላይ ግን ከተማዋ የህዝብ ቁጥር ያሉባት በመሆንዋ የተሰሩት ስራዎች ለመዝናኛነት የሚውሉ ናቸው ብለዋል። የወንዞች እና የወንዞች ዳርቻ ልማት ያደጉ አገሮች ያሟሉትን ስታንዳርድ ይዞ የተሰራ ነው መሆኑን ነው የገለፁት ።
የኢትዮጰያ ሕገ-መንግስቱ መሰረት ዜጎች በንጹህ እና ጤናማ በሆኑ ስፈራዎች የመኖር መብት እንዳላቸው ይደነግጋል ያሉት አቶ አሰግደው፣ ስለሆነም የዜጎችን መብት ጭምር ሊያረጋግጥ የሚችል ፕሮጀክት እየተተገበረ መሆኑን ጠቁመዋል። ዲስ አበባ በአለም አቀፍ ደረጃ ሶስተኛዋ የዲፕሎማት ከተማ እንደመሆኗ መጠን የሚጠበቅባትን የአረንጓዴ መሰረተ ልማት ለማሟት እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ማሳያ ናቸው ብለዋል።
በሔለን ተስፋዬ