በ2018 በጀት አመት ከ6 ሺህ በላይ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን ለማቋቋም እና ከ393 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር መታቀዱን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ አበባ ታመነ የተቋሙን የ2017 በጀት አመት አፈጻጸም እና የ2018 በጀት አመት ዕቅድ በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በተጠናቀቀው 2017 በጀት አመት በተኪ ምርት፣ በወጪ ምርት፣ በአምራች ኢንዱስትሪ በተፈጠረ የሥራ ዕድል፣ በማምረት አቅም አጠቃቀም አበረታች ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።
በበጀት አመቱ የተገኘውን ውጤት በ2018 በጀት ዓመት አጠናክሮ ለማስቀጠል በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በዚህም ተቋማዊ አደረጃጀትና ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር አንዲሁም በመሰረት ልማት ዝርጋታና ግብዓት አቅርቦት ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቅሰዋል።
በዚህም በ2018 በጀት አመት የማምረት አቅም አጠቃቀም ከነበረበት 65 ነጥብ 02 በመቶ ወደ 70 በመቶ ለማሳደግ መታቀዱን ተናግረዋል።
የውጭ ምንዛሬ ግኝት ከነበረበት 318 ነጥብ 279 ሚሊየን ዶላር ወደ 450 ሚሊየን ዶላር ለማድረስ መታቀዱን ገልጸዋል።
ተኪ ምርት በተጠናቀቀው አመት ከነበረበት 4 ነጥብ 534 ቢሊየን ዶላር ወደ 5 ነጥብ 689 ቢሊየን ዶላር ለማሳደግ ዕቅድ መያዙን ማስታወቃቸዉን ኢዜአ ዘግቧል።
6 ሺህ 178 አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን ለማቋቋም እና ለ393 ሺህ 178 ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር መታቀዱን ጠቅሰዋል።