አሜሪካ የቪዛ ባለቤቶች ወደ ሀገሪቱ ለመግባት ወይም ለመቆየት የሀገሪቱን ህግ ጥሰው እንደሆነና እንዳልሆነ ለማረጋገጥ የ55 ሚሊየን ሰዎችን ቪዛ ልትመረምር መሆኑን አስታውቃለች፡፡
የአሜሪካ ቪዛ የያዙ ሰዎች ቀጣይነት ያለው ምርመራ እንደሚደረግባቸው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ መግለፃቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ቪዛ ያላቸው ሰዎች እላፊ የመቆየት፣ የወንጀል ተሳትፎ፣ ለህዝብ ደህንነት ስጋትነት የሆኑ እና በማንኛውም ዓይነት የሽብር ድርጊት ተሳትፎ ወይም አሸባሪ ድርጅት መርዳታቸውን የሚያሳዩ ምልክቶች ካሉ ቪዛው እንደሚሰረዝ ነው ባለሥልጣኑ የገለጹት፡፡
ፀረ-ስደተኞች አቋምን የሁለተኛው የአስተዳደር ዘመናቸው የማዕዘን ድንጋይ ማድረጋቸው የሚነገረው ፕሬዚዳንት ትራምፕ፣ በዚህም ብዙዎች በጅምላ ከሀገር እንደተባረሩ፣ በአንዳንድ ሀገራት ላይ ሙሉ በሙሉ የጉዞ ክልከላ እንደተጣለ እና የ6 ሺህ ተማሪዎች ቪዛ መሰረዙን ዘገባው አያይዞ ገልጿል፡፡
በታምራት ቢሻው