“አዲስ አበባ ለነዋሪዎቿምቹ፣ ለጎብኚዎቿ ሳቢሆናለች”

You are currently viewing “አዲስ አበባ ለነዋሪዎቿምቹ፣ ለጎብኚዎቿ ሳቢሆናለች”

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ ከተማ እንደ ስሟ እያበበች ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ለጐብኚዎቿ ሳቢ ሆናለች ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ተናገሩ፡፡

ከንቲባ አዳነች ይህን ያሉት በትናንትናው ዕለት በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች የገበያ ማዕከላትን፣ የመኪና ማቆሚያዎችን እና ተርሚናሎችን መርቀው ለአገልግሎት ክፍት ባደረጉበት ወቅት ነው፡፡

ከንቲባዋ በዕለቱ ባደረጉት ንግግር “በቀድሞዋ አዲስ አበባ ይከናወኑ የነበሩ በጣት የሚቆጠሩ ዓለም አቀፍ ኩነቶች በመጡ ቁጥር የከተማዋን የተጎሳቆሉ ገፅታዎች፣ የተበከሉ አካባቢዎች፣ አንገት አስደፊ ገፅታዎች በጥቅሉ ገመናችንን ሌሎች እንዳያዩት በረጃጅም ባነር የመሸፈን ታሪክ በልጆቿ የሌት ተቀን ትጋትና በነዋሪዎቿ ትብብር ታሪክ ሆኗል።” ብለዋል፡፡

የተመረቁት ፕሮጀክቶች በከተማዋ የመንገድ ትራፊክ መጨናነቅ በነበረባቸው እና የቆሸሹ እና የተጎሳቆሉ ቦታዎችን በማጽዳት እና የትራፊክ እንቅስቃሴውን ማሳለጥ የሚያስችሉ እና የስራ እድልን ጭምር የሚፈጥሩ መሆናቸውን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።

በአራዳ፣ በሜክሲኮ፣ በለገሀር እና ሳር ቤት የአፍሪካ ህብረት አካባቢ የሚገኙና የከተማዋን ገፅታ ይበልጥ የሚያሻሽሉ፣ ለወጣቶችና ሴቶች ሰፊ የስራ ዕድል የሚፈጥሩ፣ የትራፊክ ፍሰቱን እሚያሳልጡ፣ የሚያዘምኑ፣ የአካባቢዎቹን ውበት የሚጨምሩ ፕሮጀክቶችን ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር መርቀን ለአገልግሎት ክፍት አድርገናልም ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ከሜክሲኮ እስከ ለገሀር ባለው አካባቢ ብቻ 2 ሺህ 145 ተሽከርካሪዎችን በአንድ ጊዜ ማቆም የሚችሉ 13 የተሽከርካሪ ማቆሚያዎች እና 1 ሺህ 624 ታክሲና አውቶብስ በአንድ ጊዜ ማስተናገድ የሚችሉ መጫኛ እና ማውረጃዎች ለአገልግሎት ክፍት ተደርገዋል፡፡

የአፍሪካ ህብረት የገበያ ማዕከልና ፓርኪንግ ለዲፕሎማሲው ማህበረሰብ የተለያዩ የስጦታና የባህል መሸጫዎችን በአቅራቢያው እንዲያገኙ የሚያስችሉ ሲሆን፣ በ28 ሺህ 500 ሜትር ስኴር ላይ የተገነባ ዘመናዊ ማዕከል ነው፡፡ ሁለት ቤዝመንትና ፕላዛ፣ 250 ሱቆች እና 250 መኪኖችን በአንድ ጊዜ ማስተናገድ የሚያስችል፣ በተጨማሪም የህጻናት መጫወቻ እና ማረፊያዎች፣ 45 መጋዘንና የመጸዳጃ ክፍሎች፣ ፋውንቴን፣ አምፊ ቴአትር እና ፕላዛ በውስጡ ይዟል።

ሌላኛው ባሻ ወልዴ ችሎት ጋር የተሰራው ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያና ገበያ ማዕከል ሲሆን፣ በተመሳሳይ ካፍቴሪያዎች፣ ሱፐርማርኬት፣ ሱቆች፣ ሬስቶራንቶች፣ ፕላዛ እና 200 የመኪና ማቆሚያ በውስጡ የያዘ ነው። ሁለቱም ማዕከላት ዘመናዊ የእሳት አደጋ መቆጣጠሪያና የደህንነት ካሜራ የተገጠመላቸው ሲሆን፣ ለህፃናት፣ ለአቅመ ደካሞችና አረጋውያን ምቹ ሆነው የተሰሩ ስለመሆናቸው ተገልጿል፡፡

በጥቅሉ ከሜክሲኮ እስከ ለገሀር እና አፍሪካ ህብረት ዙሪያ ባሉ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ 13 የመኪና ማቆሚያና፣ 10 ተርሚናሎች እስከ 3 ሺህ 769 ተሽከርካሪዎችን ማስተናገድ የሚችሉ የፓርኪንግ እና ተርሚናል መሰረተ ልማቶች ጭምር ይገኙበታል ተብሏል።

የተሽከርካሪ ማቆሚያዎቹና የታክሲና የአውቶብስ መጫኛ እና ማውረጃዎቹ 300 የሚደርሱ ሱቆች፣ 50 መጋዘኖች፣ 80 የሚደርሱ መጸዳጃ ቤቶች፣ የደህንነት ካሜራዎች፣ ከአንድ ማዕከል ቁጥጥር ለማድረግ የሚያስችሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የተሟሉላቸው ናቸው፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባስተላለፉት መልዕክት፣ እነኚህ ለከተማዋ እድገት ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው ፕሮጀክቶች በታለመላቸው ጊዜ እና በጀት እንዲጠናቀቁ ሌት ተቀን ለደገፉ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና የአካባቢው ማህበረሰብ ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ከተሽከርካሪ ማቆሚያዎች እና የገበያ ማዕከላት በተጨማሪ የታክሲና የአውቶብስ መጫኛ እና ማውረጃዎች ተመርቀው ስራ የጀመሩ ሲሆን፣ በዚህ ክረምት ወደ 19 ሺህ የሚጠጉ ፕሮጀክቶች ተገንብተው ወደ አገልግሎት እየገቡ ስለመሆኑ ተነግሯል፡፡

በቅርብ ጊዜም በመዲናዋ 4 ኪሎ ፕላዛ፣ 4 ኪሎ የገበያ ማዕከል እና መኪና ማቆሚያ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት መደረጉ ይታወሳል። ፕሮጀክቱ ከመሬት በታች የተገነቡ እጅግ ዘመናዊ 102 የስጦታ እና የአልባሳት መደብሮች፣ ካፍቴሪያዎች፣ ማንበቢያ ስፍራዎች፣ ሱፐር ማርኬቶች፣ ከ100 በላይ ተሽከርካሪዎችን በአንድ ጊዜ የሚያስተናግድ የመኪና ማቆሚያ እና በአንድ ጊዜ እስከ 5 ሺህ ሰዎችን መሰብሰብ የሚያስችል የፕላዛ፣ የአንፊ ቴአትርና የተለያዩ የጥበብ ስራዎችን ማቅረቢያ ስፍራዎችን የያዘ እና ከወዲሁ ከ500 በላይ ለሚሆኑ ወጣቶችና ሴቶች የስራ ዕድል የፈጠረ እንደሆነም ይታወቃል፡፡

በሳህሉ በርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review